News Detail
May 23, 2025
104 views
የአፍሪካውያ ችግር በአፍሪካውያን መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ፤ በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የ2025 የኢራስመስ ጉባኤ ተጠናቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የአፍሪካ አገራትን ትብብር በማጠናከር የአፍሪካውያውያን ችግሮችን በአፍሪካውያን መፍታት ይገባል ብለዋል።
አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን ለመፍታት በትብብርና በቅንጅት አጽንኦት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመንግስት የሚመደበውን በጀት ከመጠቀም ባሻገር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተልዕኳቸውን ማሳካት እንዳለባቸውና በኢራስመስ ፕሮግራምንና የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን በመጠቀም ለሀገር ልማትና ብልጽግና መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ክቡር አቶ ኮራ ጨምረው አስገንዝበዋል፡፡
በብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የትምህርት፣ ስልጠና፣ ባህልና ሳይንስ ዳይሬክተር ጄኔራል ክሌር ሄርማን የኢራስመስ ፕሮጀክት ለአፍሪካውያን እጅግ በጣም ጠቃሚ መሆኑንና አፍሪካውያን ፕሮግራሙን በአግባቡ በማስተዋወቅና በማስፋት መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ጉባዔ እጅግ በጣም ጠቃሚ እንደነበርና ብዙ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን አንስተው በአግባቡ በመጠቀም እንደ ሀገር የተለዩ የሪፎርም ስራዎችን ማሳካት እንደሚገባና እንደ አፍሪካ በትብብር ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተካሄደው በዘንድሮው የኢራስመስ 2025 ጉባኤ ከሰሃራ በታች የሚገኙ 32 የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ ከ46 አገራት የተወከሉ ጉባኤተኞቾ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡