News Detail
May 22, 2025
91 views
የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በለንደን እየተካሄደ ባለው አለም አቀፍ የትምህርት ፎረም 2025 ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራ ልኡካን ቡድን በለንደን እየተካሄደ ባለው አለም አቀፍ የትምህርት ፎረም 2025 ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ እየተካሄደ ካለው የትምህርት ፎረሙ ጎን ለጎን ከእንግሊዝ የአለምአቀፍ ልማት ሚኒስትር ባሮነስ ቻፕማን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም ክቡር ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም የገልጹላቸው ሲሆን በራስ አቅም በ “ትምህርት ለትውልድ’’ ህዝባዊ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻን በተመለከተ ስለተገኘው ውጤት አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሥርዓተ ትምህርት፣ ከመምህራንና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ስልጠና እና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጋር በተያያዘ የተጀመሩ ሥራዎችን ጠቅሰው፣
እነዚህ በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ ሪፎርሞች በፍጥነት እንዲሳኩ የልማት አጋሮችና በተለይም የእንግሊዝ መንግስት ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የእንግሊዝ የአለምአቀፍ ልማት ሚኒስትሯ ባሮነስ ቻፕማን በበኩላቸው በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደርጉትን ጉብኝት በማስታወስ በትምህርት ዘርፉ እየተደረገ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል፣
የተጀመረውን የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ ምንም እንኳን በእንግሊዝ መንግስት የተደረገው የበጀት ቅነሳ (budget cuts) ቢኖርም በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የሚካሄደውን ሪፎርም ለመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ክቡር ሚኒስትሩ ከተለያዩ አገራት የትምህርት ሚንስትሮች ጋር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም በተመለከተ ውይይቶች አድርገዋል።
በዚህ ዓለም አቀፍ የትምህርት ፎርም ላይ ከ150 በላይ የትምህርት ሚኒስትሮች የሚመራ የልዑካን ቡድን እየተሳተፈ እንደሚገኝም የተገለጸ ሲሆን፣
ክቡር ሚኒስትሩም በዓለም አቀፉ የትምህርት ፎረም ላይ ‘’ የገንዘብ ድጋፍን ማሻሻል፣ ውጤታማ እቅድ በማውጣትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት ረገድ አንዳችን ከሌላችን ምን እንማራለን?’’ በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የመነሻ ፅሁፍ አቅርበዋል።