News Detail

National News
May 30, 2025 70 views

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል እድል አግኝቶ የሚማርበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ የትምህርት ሚኒስትሩ ገለፁ።

በጋምቤላ ክልል በሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት ለሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በየአካባቢው መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም በጋምቤላ ክልል የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትምህርት ጥራት ችግርና የመማሪያ ክፍል ጥበት ለመቅረፍ የዚህ ትምህርት ቤት ግንባታ መጀመር አስተዋጸኦ የጎላ ይሆናል ብለዋል።
አክለውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል እድል አግኝቶ የሚማርበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ሰፊ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በዚህም በመላ ሀገሪቱ 31 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 15ቱ በትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም 16ቱ ደግሞ በሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት እንደሚገነቡ አንስተው በተለይም በቂ የመሰረተ ልማት ባልተሟላላቸው ክልሎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው ይህ ትምህርት ቤት በክልሉ የትምህርት ጥራት መረጋገጥ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በክልላችን የተመዘገበውን ዝቅተኛ የተማሪ ውጤት ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ፈተናዎች ማለፍ የሚቻለው ዘመኑ የሚጠይቀውን ክህሎት የተላበሱ፣ ችግር ፈቺ ፣ ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ሲቻል መሆኑን አንስው፤
የትምህርት ጥራት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በክልሉ የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የዚህ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ሙሉ ወጪ በሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት እንደሚሸፈን የተገለፀ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃልም ተብሏል።
በዚህም ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትል ለማድረግ በትምህርት ሚኒስቴርና በክልሉ ትምህርት ቢሮ መካከል የሥምምነት ፊርማ ተከናውኗል።
Recent News
Follow Us