News Detail
Aug 04, 2025
69 views
በአገሪቱ በተመረጡ 30 ዩኒቨርስቲዎች የሚሰጠው የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና መሰጠት ጀመረ። በስልጠናው ከ84 ሺ የሚበልጡ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ይሳተፋሉ፡፡
ስልጠናውን መስጠት ከጀመሩ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትምህርትና ቋንቋዎች ጥናት ኮሌጅ ኤክስኪዩቲቭ ዲን የቆየዓለም ደሴ (ዶ/ር) ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን በጥሩ ሁኔታ ለማሰልጠን የአሰልጣኝ መምህራን ፣ የስልጠና ክፍሎች፣ የተማሪዎች ማደሪያ ፣ የካፍቴሪያ እና የማሰልጠኛ ሞጁልና ምዝገባ አጠናቆ ስልጠና መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው መምህራን በሚያስተምሩበት ትምህርት ዓይነት ፣ በማስተማር ስነ ዘዴ፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም በስነ ልቦናዊ ፣ ማህበራዊና የጤና ጉዳዮችን አካቶ የያዘና ሰፊ ክፍተትን የሚሞላ በመሆኑ ሰልጣኞች ተረጋግተው መሰልጠንና የመጡበትን አላማ ሳይረሱ ክፍል ውስጥም ሆነ ከሌሎች ጓደኞቻቸውና ከአሰልጣኝ መምህራን ጋር መነጋገር እና መማር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው ያገኘናቸው የስልጠና አስተባባሪ አቶ ታደሰ ተሬሳ በበኩላቸው ለሰልጣኝ የ2ኛ ደረጃ መምህራንና የት/ቤት አመራሮች በዩኒቨርስቲው አቀባበል እንደተደረገላቸው ጠቁመው ሰልጠናውንም በሚመለከት ገለጻ የተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ስልጠናው የመመህራኑንና አመራሮቹን አቅም በማጎልበት የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻልና በትምህርት ላይ ያሉ ቸግሮችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስልጠናው ላይ የገኘናት የፋና 02 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ መምህርት ኩመሌ አበራ በሰጠችው አስተያየት ስልጠናው ከዚህ በፊት ከነበራት እውቀትና ክህሎት በተጨማሪ ተጨባጭ እውቀት ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፣ የማስተማር ስነ ዘዴ ክህሎት አገኛለሁ ብላ እንደምትጠብቅ ተናግራለች፡፡
የጣፎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ዘውዲቱ ሰቦቃ በበኩሏ ባለፈው ዓመት የሰለጠኑ መምህራን የማስተማር ተነሳሽነትና ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሳ ስልጠናው ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላትና ተነሳሽነቷንም የበለጠ እንደሚያሳድግላት ገልጻለች፡፡
የቀራንዮ አንደኛና መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርአሰ መምህር አህመድ በዳሶ በዚሁ ጊዜ በሰጠው አስተያየት ስልጠናውን በሙሉ ልብ ለመውሰድ ሰው ወክሎና አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ መምጣቱን ገልጾ ከስልጠናው ብዙ ለውጦችን አግኝቶ ክፍተቱን እንደሚሞላ ተናግሯል፡፡