News Detail
Aug 06, 2025
102 views
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሁሉም ክልሎች የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን እንደ አንድ የሀገር ልጆች የሚቀበልበት የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮግራም ለጎንደር ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ምሳሌ የሚሆን መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ገለፁ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና ማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷ።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይህ ክብረ በዓል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለጎንደርና ለአካባቢው ህዝብ ያለውን ፋይዳ እንዲሁም ህዝቡ ለተቋሙ ያለውን አክብሮት ያየንበት ነው ብለዋል።
በዓሉ ከዩኒቨርሲቲውና ከሆስፒታሉ ምስረታ በላይ በተለይ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የጎንደርን ህዝብ ጥልቅ የሆነ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያንፀባረቀበትም እንደነበር አንስተዋል።
በተለይም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሁሉም ክልሎች የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን እንደ አንድ የሀገር ልጆች የሚቀበልበት “የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮግራም” ለጎንደር ብቻ ሳይሆን ለሀገራችንም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ዩኒቨርስቲዎች አንዱ እንዲያደርጉ የምንፈልገው የመንደር ሳይሆኑ የሀገር ሀብት እንዲሆኑ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፤
በተለይ አሁን ዋና ሪፎርም ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲችሉ በነፃነት የሚሰሩ፣ በነፃነት የሚያስቡ እውነትንና እውቀትን የሚፈልጉ ሰዎች የተሰባሰቡባቸው ሰላማዊ ቦታ እንዲሆኑ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ዩኒቨርስቲዎች በመማር ማስተማር ፣ በጥናትና ምርምር በሚሰሩ ሥራዎች አካባቢያቸውን እንዲረዱ እና የአካባቢውን ፀጋ ተጠቅመው የህዝቡን ህይወት እንዲያሻሽሉ ይጠበቃል ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው 70ኛ እና ማስተማሪያ ሆስፒታሉ 100ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ከጥር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ኩነቶች ሲከበር ቆይቶ በስኬት መጠናቀቁን በመግለጽ ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ጀምሮ ያከናወናቸውን የታሪክ ጉዞ ያነሱት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ዩኒቨርስቲው ራስ ገዝ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል ።