News Detail
Aug 01, 2025
33 views
ለሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ የክረምት ስልጠና የዩኒቨርስቲ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አሳሰቡ፡፡ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ከ84ሺ የሚበልጡ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች በ30 ዩኒቨርስቲዎች ስልጠና እንደሚወስዱም ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ በሰጡት ማሳሰቢያ ለሁለተኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና ስኬታማነት የዩኒቨርስቲ አመራሮች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን ስልጠና የሚሰጡ 30 ዩኒቨርስቲዎች ሰልጣኝ መምህራንንና የትምህርት ቤት አመራሮችን በአግባቡ በመቀበልና በማሰልጠን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
አክለውም የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና ለትምህርት ጥራት ወሳኝ በመሆኑ ዩኒቨርስተዎች መምህራኑና አመራሮቹ የተዘጋጀላቸውን የስልጠና ሞጁል መጨረሳቸውን ፣ስልጠናውንም በአግባቡ መከታተላቸውንና መመዘናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ስልጠና በአግባቡ እንዲጠናቀቅ የዩኒቨርስቲ አመራሮችና ኃላፊዎች ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣቱ ከ84ሺ የሚበልጡ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች በሚያተምሩት የትምህርት ዓይነት ላይ መሰረት ያደረገ ስልጠና ወስደው ከተመዘኑ በኋላ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው በመድረኩ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ከ52 ሺ የሚበልጡ የ2ኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ የክረምት ስልጠና መውሰዳቸውንም ይታወሳል፡፡