News Detail

National News
Jul 16, 2025 40 views

የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከባለፉት ሶስት አመታት በተሻለ መልኩ በሠላም እና በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።

የትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የታለመለትን ግብ በመምታት በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን የትምህርት ሚንስትሩ ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።
ሚንስትሩ የነበረውን የፈተና አሰጣጥ ሂደት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት ሶስት አመታት በተወሰነ መልኩ ያጋጥሙ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች፣ የፈተና ስርቆት ሙከራዎች፣ የፈተና ስርዓትና አስተዳደር የዲሲፒሊን ግድፈቶች በዘንድሮው አመት ቀንሰው መገኘታቸውን አብራርተዋል።
ለዚህም የበይነ መረብ የፈተና ሽፋን በአንድ አመት ውስጥ በአራት እጥፍ ማደጉ፤የፈተና ግብረ ሀይሉ ያልተቆጠበ ጥረት፤ እንዲሁም ተማሪዎች ሰርቶ ውጤት ማምጣት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን መገንዘባቸውና መሰል ለውጦች ችግሮች ጎልተው እንዳይስተዋሉ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ በበኩላቸው ፈተናው በአራት ዙሮች እንዲሠጥ የተደረገ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በአራቱም ዙሮች የተሰጡ ፈተናዎች ተቀራራቢ (አቻ) መሆናቸውን አብራርተዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን በአጠቃላይ ከተመዘገቡ ተፈታኞች 608,742 መካከል 581,905 (95.6%) ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 134,828 (23.2%) በበይነ መረብ ብቻ የተፈተኑ መሆናቸው ተብራርቷል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአማራ ብሔራዊ ክልል ያሉ እና የተወሰኑ የህግ ታራሚዎች በድምሩ 4,966 ተፈታኞች ከነሐሴ 26-28/2017 ዓ/ም በሁለተኛ ዙር የተዘጋጀላቸውን ፈተና በወረቀት የሚወስዱ መሆኑንም አያይዘው አሳውቀዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን በበይነ መረብ የተፈተኑ ተፈታኞች ቁጥር 29,727 ብቻ የነበረ ሲሆን በዘንድሮ አመት ወደ 134,825 መድረሱ ከፍተኛ ስኬት መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል።
በመጨረሻም በፈተና አሰጣጥና አስተዳደር ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን ላበረከቱ ሁለ የትምህርት ሚኒስቴር ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ብሏል።
Recent News
Follow Us