News Detail
Jul 10, 2025
86 views
በአገሪቱ ተመጣጣኝና ፍትሃዊ የትምህርት ዘርፍ ልማትን ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ፡፡ የትምህርት ቤቶችን ሥርጭት የሚያሳይ የዲጂታል ካርታ የትምህርት ሚኒስትሩ በተገኙበት ይፋ ሆኗል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በሀገሪቱ ተመጣጣኝ የሆነ የትምህርት ዘርፍ ልማትን ለማምጣት ትምህርት ቤቶች ግልጽና ትክክለኛ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ እንዲገነቡ የሚያስችል ዲጅታል የትምህርት ቤቶች ስርጭት የሚያሳይ ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በነበረው አሰራር የትምህርት ቤቶች ግንባታ ምርጫ የሚወሰነው በገለልተኝነትና በበቂ መረጃ ሳይሆን በዘር ፣ በትውወቅና ፖለቲካዊ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ እንደነበረም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም በአዲሱ ስርዓት ማንኛውም በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ፍላጎት ያለው ሰውም ሆነ ለጋሽ ድርጅት የትኛውንም የመንግስት ባለስልጣን ወይም ተጽእኖ ፈጣሪ መጠየቅ ሳያስፈልገው በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ትምህረት ቤቶችችን መገንባት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
አክለውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የትምህርት እድል ማግኘት እንዳለበት አንስተው ለሁሉም ዜጎች ትምህርትን በፍትሃዊነት ለማድረሰ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራትና ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ ወጋሶ( ዶ/ር) በበኩላቸው ይፋ የሆነው የትምህርት ቤቶች ስርጭት ካርታ ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው የትምህርት ቤቶችን ወቅታዊ ስርጭት፣ የመሰረተ ልማት፣ የህዝብ ብዛት እና ሌሎች መረጃዎችንም አካቶ የያዘ መሆኑ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ለጋሾችም ሆኑ ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻዎች መረጃውን በመጠቀም ትምህርት ቤቶችን መገንባትና የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በዚህ የትምህርት ስርጭት ካርታ ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት በተዘጋጀው ስታንዳርድ መሰረት ሲሆን የት ይገነባሉ የሚለውን ምላሽ የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩ ላይም የትምህርት ልማት ሥራ አጋር የሆኑ የውጪና የሀገር ውስጥ ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።
Recent News
Jul 11, 2025