News Detail

National News
Sep 15, 2025 41 views

የ2018 ዓ.ም ትምህርት መማር ማስተማር ስራ በመላ ሀገሪቱ ተጀምሯል። የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሂደቱን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።

የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ አዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው የ2018 የትምህርት ዘመን አጀማመርን ምልከታ ባደረጉበት ወቅት በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማሩን ስራ በማሻሻል ተማሪዎች በቂ እውቀት እና ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ ውጤታማነታቸው እንዲሻሻል ሁሉም አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ተማሪዎችም ለትምህርታቸው ትኩረት በመስጠት ማጥናትና ጊዜያቸውን በፕሮግራም ለትምህርት ስራ ማዋል እንደሚጠበቅበቸው ተናግረዋል፡፡
መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችም በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች የሚሰጡትን እውቀት በላቀ ደረጃ በማሳደግ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የተማሪዎች ስነ ምግባር ለትምህርት ስራ ወሳኝ በመሆኑ ተማሪዎች በሰነ ምግባር የታነጹ በአለባበሳቸውና በስነ ምግባራቸው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ ክብርት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች አስገንዝበዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድም ትምህርት ቤቶች ፣ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ የየአካባቢው ማህበረሰብና ሌሎችም የዘርፉ ባለድርሻዎች አስተዋጽኦ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ተዘዋውረው ምልከታ ባደረጉባቸው ትምህርት ቤቶች የ2018 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ በጥሩ ሁኔታ መጀመሩን ማረጋገጥ መቻላቸውንም ክብርት ወ/ሮ አየለች ጨምረው ተናግረዋል።
 
Recent News
Follow Us