News Detail

National News
Feb 08, 2026 15 views

አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የለውጥና መደበኛ ስራዎች አፈጻጸም ሂደት የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተጠቆመ።

የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመግም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በዚህም የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተጀመረበትን ግለት ጠብቆ በህብረተሰቡ ዘንድ መቀዛቀዝ እንዳይኖር እስከመጨረሻው እንዲቀጥል በቁርጠኝነት መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በተለይም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለማስፋፋት የተሰራው ሥራ የሚደነቅ ሲሆን የበለጠ በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የአመራር አጀንዳ አድርጎ በቁርጠኝነት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህም ባለፈ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥን ከመቀነስና ውጤታማነትን ከማረጋገጥ አኳያ የትምህርት ቤት ምገባን በበጀት በመደገፍ፤ ሀብት በማሰባሰብ እንዲሁም ማህበረሰቡን በስፋት በማሳተፍ ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ አመላክተዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በተደረገው የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ትግበራ መሠረት የመጽሐፍት አቅርቦት ላይ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ አሁንም የተማሪ መፅሃፍትን አንድ ለአንድ የማድረስ ሥራ በተለይም ከቅድመ አንደኛ እስከ አንደኛ ደረጃ የክልሎችን ትኩረት የሚፈልግ በመሆኑ በፍጥነት መፈፀም ይገባል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም መገንባትና አማራጭ የመምህራን ስልጠናን እንደ አንድ የትኩረት መስክ በመያዝ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በቅድመ-አንደኛ ደረጃና በመሠረታዊ የጎልማሶች ትምህርትና ክህሎትን ለማሳደግ የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎችን በስፋት ለማስቀጠል አመራሩ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እየተወሠዱ ካሉ እርምጃዎች አንዱ የሆነው የማጠናከሪያ ትምህርት (Tutorial) በማጠናከር በቅርብ መከታተል እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የታቀዱ ግቦች እንዲሳኩ የተቀናጀ የአመራር ሚና እና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ፣ በየደረጃው የሚገኘው አካል ለተግባራዊነቱ በትጋት መስራት እንደሚገባው ክብርት ሚኒስቴር ዴኤታዋ አሳስበዋል።
Recent News
Follow Us