News Detail
Sep 18, 2025
45 views
የትውልዱን ስኬታማነት ለማረጋገጥ በኤችኣይቪ ኤድስና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በሀገሪቷ ለሚገኙ የመምህራን ኮሌጆች የተለያዩ ክበብ ተጠሪ መምህራን ጋር ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች ልማት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አሰግድ መሬሳ የወጣቱን ትውልድ ሁለንተናዊ ስኬታማነት ለማረጋገጥ በኤችኣይቪ ኤድስና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማነት የሚረጋገጠው በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን በተጓዳኝ በሚሰጡ የህይወት ክህሎት ሥልጠናዎችና እውቀቶች መሆኑን ጠቅሰው የኮሌጅ መምህራን የተጓዳኝ ትምህርት ክበባት በሚገባ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የብሄራዊ ዩኔስኮ ዋና ጸሃፊ አቶ አለሙ ጌታሁን በበኩላቸው በህይወት ክህሎት ሥልጠና እጥረት ምክንያት የኤችአይቪ ኤድስና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች የወጣቱ ትውልድ ስጋት ሆነው መቀጠላቸውን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ጠቅሰው የመምህራን ኮሌጆች ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አክለውም በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ነባራዊ ሁኔታን መሠረት ያደረገ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ክበባት በውጤታማነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሥልት የሚቀመጥም መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሌጅ መምህራኑም ወደየ መጡበት ሲመለሱ በኤች አይቪና ስነተዋልዶ የሚሰሩ ክበባትን እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የማጠናከር ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል።