News Detail
Oct 22, 2025
185 views
በትምህርት ዘርፉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የቅሬታ አፈታት ስርዓቶች አበረታች መሆናቸው ተገለጸ፡፡ የትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እና የቅሬታ አፈታት ስራ ክፍል ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ በትምህርቱ ዘርፉ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የቅሬታ አፈታት አሰራር ስርዓቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን የተዘረጉ የአደረጃጀትና የአሠራር ስርዓቶች በትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የቀረበውን የውይይት መነሻ ሀሳብ በመንተራስ ሀሳባቸውን ያጋሩት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በየደረጃው ባለ መዋቅር የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ቅሬታዎችን ለመፍታት የተለያዩ አደረጃጀቶችና የአሰራር ስርዓቶችን ወደ ተግባር በማስገባት ተገልጋዬችን ከዕንግልት፣ ከተጨማሪ የጊዜና ገንዘብ ወጪ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።
አሳታፊነት ከማጠናከርና ከማረጋገጥ አኳያ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በጋራ የማቀድ፣ የመከታተል፣ የመገምገምና ግብረ መልስ የመስጠት ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ክብርት ወ/ሮ አየለች አያይዘው ገልጸዋል ።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉና የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና የቅሬታ አፈታት ስርዓቶችን ለማሻሻል በመከናወን ላይ ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል።
በተማሪ ቅበላ ፣ በፈተና አስተዳደር፣በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎችና ቅሬታዎችን ቀድሞ የማወቅና የመከላከል ተግባራት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደር ጉዳዬችና የቅሬታ አፈታት መሪ ስራ አስፈጻሚ ፍቅሩ ወርቁ በበኩላቸው በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉና የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ለመከላከልና ለመፍታት በመከናወን ላይ ያሉ የአደረጃጀትና የአሠራር ስርዓቶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የስራ ሀላፊው አያይዘውም በትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በኩል የተዘረጉት የመልካም አስተዳደርና የቅሬታ አፈታት አደረጃደትና አሠራር ስርዓቶች ለሌሎች ተቋማት ተሞክሮና ልምድ የሚቀሠምባቸው መሆኑን አመላክተዋል።