News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 22, 2025 42 views

በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሀገራዊ ምክክር መድረክ የ2018 ዓ.ም የቁልፍ ተግባራት ውጤት አመላካች መለኪያዎች ላይ የጋራ ስምምነት በመፈራረም ተጠናቋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ለሁለት ቀናት በሀዋሳ ከተማ ሲያካሄድ የነበረው የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሀገራዊ የምክክር ከሁሉም የክልልና ከተማ መስተዳድር ቢሮዎች ጋር የ2018 ዓ.ም የቁልፍ ተግባራት ውጤት አመላካቾችን የስምምነት ሰነድ በመፈራረም አጠናቋል።
መድረኩ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በጥልቀት የተመከረበትና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከመግባባት የተደረሰበት መሆኑ ተመላክቷል።
በመድረኩ የተገኙት የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ የትምህርት ተሳትፎ፣ ጥራትና ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ ረገድ በ2017 የትምህርት ዘመን የተገኙ ስኬቶችን በማስፋትና በማስቀጠል በመጭው አመት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መድረኩ በመምከር አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በዘርፉ የአፈጻጸም ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች በመሻገር በ2018 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረትም እንዲሁ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የተመከረበት እንደሆነም ክብርት ሚንስትር ዴኤታዋ አያይዘው ገልጸዋል።
የትምህርት ለትውልድ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የቅድመ አንደኛ ትምህርት፣ የስርዓተ ትምህርት ትግበራ፣ የመምህራንና የትምህርት አመራር አቅም ግንባታ፣ ዲጂታይዜሽን እንዲሁም የወንድና ሴት ተማሪዎችን ምጥጥን አስጠብቆ የመሄድና ሌሎች መሰል የሪፎርም ስራዎች ላይ ሁሉም የክልልና ከተማ መስተዳድር ት/ቢሮዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል።
በመጨረሻም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተዘጋጁ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ደንቦቹ ሀገራዊ ሁኔታውንና የህዝብ ፍላጎትን ያማከሉ እንዲሆኑ በቀጣይ ግብዓት የማሰባሰብ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
Recent News
Follow Us