News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 26, 2025 94 views

የትምህርት አገልግሎትን ከትርፍ ጋር ብቻ አያይዞ መሥራት ሀገርን እንደሚጎዳ ተገለጻ፡፡

የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ አገልግሎት እየሰጡ ባሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ባካሄደው የዳግም ምዝገባ አፈጻጸም ዙሪያ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት አገልግሎትን ከትርፍ ጋር ብቻ አያይዞ መሥራት ሀገርን እንደሚጎዳ ገልጸዋል፡፡
መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናው ጥናት መሠረት በተካሄደውና በቀጣይ በሚካሄደው ምዘና ዝቅተኛ የምዘና መስፈርቶችን የማያሟሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከትምህርት ሥርዓቱ እንዲወጡ የሚደረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ከሀገር ወቅታዊና የወደፊት ፍላጎት እንዲሁም ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመቃኘት መምራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም ይህ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተጀመረው የብቃት ምዘና ሥራ ያለ ምንም ማዳላት በተመሳሳይ መልኩ በመንግሥት ተቋማት ላይም ተግባራዊ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ አብተው በበኩላቸው ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በዳግም ምዝገባና አስፈላጊነቱ ላይ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ተገቢውን መስፈርት እንዲያሟሉ ተጨማሪ ጊዜ ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል ዕድሉን ተጠቅመው መሻሻል ያሳዩ ተቋማት እንዳሉ ገልጸዋል።
በትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የተቋማት ፈቃድ አሰጣጥ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ህይወት አሰፋ ዳግም ምዝገባ ተቋማት ተዛማጅ ካልሆኑ የንግድ መስኮች ጋር ተቀላቅለው እንዳይሰሩ ፣ ህጋዊ የአሰራር ስርዓት ተከትለው እንዲሰሩ፣ በራሳቸዉ ህንጻ ወይም ሙሉ ህንጻ ተከራይተው ማስተማር እንዲችሉ፣ ሰነዶቻቸውን በአዲሱ የጥራት መስፈርት መሰረት እንዲከልሱ፣ የመምህራንን የትምህርት ዝግጅትና የቅጥር ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ እንዲያስተካክሉ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ማህበረሰብ አገልግሎት ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩ የማበረታታት እና ተቋማዊ መዋቅራቸዉን በመገምገም ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለቤቶችና ሃላፈዎች ተገኝተው ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች በከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቷል።
Recent News
Follow Us