News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Feb 23, 2026 15 views

እንደ ሀገር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ ባልሆነባቸው ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የትምህርት ቤት ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለሟሟላትና ለማሻሻል በቀረጸው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል።
በተለይም ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ትኩረት በመስጠት እና በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ነጻና የግዴታ ትምህርት እንዲሆን በማመላከት ከ34000 በላይ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት እነዚህ ትምህርት ቤቶች ቢገነቡም የነበረውን ክፍተት በሚፈለገው ልክ መሙላት ባለመቻሉ በርካታ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፤ ይንንም ለመቅረፍና ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዚህም ‎ትምህርት ቤቶቹን ለመገንባት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ ያልሆነባቸው አካባቢዎችና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ወረዳዎች ልየታ መደረጉም ተገልጿል።
በነዚህ በተለዩ ወረዳዎች ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ትምህርት ሚኒስቴር በውጤት ተኮር የገንዘብ ድጋፍ ስርዓት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ግንባታውን ለማከናወን አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
ከሚገነቡት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በተደረገው የዋጋ ጥናት 726ቱ በትምህርት ሚኒስቴር የሚገነቡ ይሆናል። እነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚገነቡት ክልሉ በተጠቀሱት ወረዳዎች ወይም አካባቢዎች ትምህርት ሚኒስቴር በሚሰራው ልክ በክልሉ በጀት ወይንም ከማህበረሰቡ አሰባስቦ መገንባት የሚችል ከሆነ ብቻ ነው።
በዚህም በቀጣይ 6 ወራት ትምህርት ሚኒስቴር 726 እንዲሁም ክልሎች በተመሳሳይ 726 በአጠቃላይ 1452 የሚደርሱ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመላ ሀገሪቱ ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ዲዛይን የተሰራ ሲሆን እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ መጠነኛ ለውጥ እንዲኖራቸው እንደሚደረግና ቢያንስ ሁለት የመማሪያ ፣ የመመገቢያ ፣ የህጻናት ማረፊያ ፣ የመምህራን ቢሮ፣ የመጸዳጃ ክፍሎችና ህጻናትን ለፈጠራ በማነሳሳት ሁለንተናዊ እድገታቸው ላይ አወንታዊ ሚና የሚጫወቱባቸው የመጫወቻ ቦታዎች እንደሚኖራቸው ተደርጎ መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።
‎የእነዚህ ትምህርት ቤቶቹ መገንባት ሁሉም የኢትዮጵያ ህጻናት አንደኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት ቢያንስ ሁለት ዓመት የቅድመ አንደኛ ደረጃ የዝግጁነት ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችላቸውም ይሆናል።
Recent News
Follow Us