News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Mar 26, 2026 10 views

በኢትዮጵያ የትምህርት ቴክኖሎጂን ለማሳደግ ያለመው የ2026 የኤድቴክ (EdTech) ሳምንት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በኢትዮጵያ የትምህርት ቴክኖሎጂ (EdTech) ዘርፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመው የ2026 የኤድቴክ ሳምንት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በደመቀ ሁኔታ ተከፍቷል።
መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱት የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ማልማትና ጥቅም ላይ ማዋል ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም የትምህርት ስራውን የሚደግፉ ቴክኖሎጂዎች የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና ያላቸው በመሆኑ በስፋት በማልማትና ተደራሽ በማድረግ ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያም የለሙ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተቋማዊ አሰራር (System) በመቀየር ረገድ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግርን ብሄራዊ አጀንዳ አድርጎ በትኩረት በማስፈጸም የማህበረሠቡን ተጠቃሚነት በመረጋገጥ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተገኙ ስኬቶችን ያመላከቱት ሚኒስቴር ደኤታው በቀጣይም ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኤድቴክ ፌሎውሺፕ ሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች የፈጠራ ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ይህም ለአዳዲስ የፈጠራ ስራ ባለቤት ለሆኑ ወጣቶች ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
ይህ "የተቀናጀ የትምህርት ቴክኖሎጂ ሁሉን አቀፍ እና የሥርዓተ-ፆታ ምላሽ ሰጪ ለሆነ ትምህርት" በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የ2026 የኤድቴክ ሳምንት በትምህርት ሚኒስቴር፣ በሪች ፎር ቼንጅ (Reach for Change) እና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ተመላክቷል።
Recent News
Follow Us