News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jun 11, 2026 38 views

በኢትዮጵያ የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርትን ለማስተማር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

በኢትዮጵያ ትምህርት የቻይንኛ ቋንቋን ለማስተማር የሚያስችል የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነት ትላንት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሃይ በጋራ ፈርመውታል።
ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይም በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በባህል ልውውጥ ዙሪያ አዳዲስ ምዕራፎችን የሚከፍት መሆኑ ተመልክቷል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ስምምነቱ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈ በቱሪዝም፣ በህዝብ ለህዝብ ትስስር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
"ዜጎቻችን የተለያዩ ቋንቋዎችን እንዲማሩ መደረጉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ትልቅ እድል ይፈጥራል" ያሉት ፕሮፌሰር ክንደያ፣ በተለይም ቻይና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ ዘርፍ የደረሰችበትን የላቀ ደረጃ እና የነፃ የትምህርት ዕድል (Scholarship) ለኢትዮጵያውያን የምታመቻችበትን ሁኔታ ለማሳለጥ ስምምነቱ መሠረት መሆኑን አብራርተዋል።
ስምምነቱ በስርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ በመምህራን ስልጠና እና በቁሳቁስ አቅርቦት ላይ የቴክኒክና የቻይና ቋንቋ መምህራንን ድጋፍ የሚያጠቃልል ሲሆን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የዕውቀት ልውውጥን እና የስኮላርሺፕ ዕድሎችንም ያሰፋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሃይ በበኩላቸው፣ ይህ ስምምነት በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፣ በአሁኑ ወቅት በቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአማርኛ ቋንቋን ማስተማር መጀመሩ የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረና በባህል ልውውጥ ረገድ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን በልዩነት አንስተዋል።
ይህ የጋራ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማጠናከሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ተማሪዎች የክህሎት አድማስ በማስፋት ለነገው ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ እና ለዲጂታል ዘመን ብቁ የማድረጉ ሂደት አካል መሆኑም ተጠቁሟል።
Recent News
Follow Us