News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Aug 04, 2025 65 views

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ። የኢትዮጵያ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት "የከፍተኛ ትምህርት ለላቀ ተፅዕኖ" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሽኔ ይህ ጉባኤ በትምህርት ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ተግባራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምን ያህል ለውጥ ተመዘገበ ተብሎ የሚገመገምበትና የወደፊት አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን ገልፀዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወዳዳሪ፣ የበለፀገች፣ ሉዓላዊት፣ ዴሞክራሲያዊት እና ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሚናቸው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም "የትምህርት ጥራት የምርጫ ጉዳይ ባለመሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በገቡት የቁልፍ ተግባራት መለኪያ ውል መሠረት ጥራትን ለማረጋገጥ በተሰሩና ባልተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ለመመካከር እድል ይፈጥራል ብለዋል።
በተጨማሪም መድረኩ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ጉባኤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 70ኛ እና የአጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የ100ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት በመሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ገልፀው ለዚህም አመሥግነዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ ለማድረግ የሚካሄደው ለውጥ የሚደነቅ መኾኑን አንስተው የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ራስ ገዝ ለመሆን እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአዲስ አሠራር እና የለውጥ ሐዋርያ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለዚህም በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ የትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኀላፊዎች ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ፤ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጅ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ የመምህራን ማኅበር የሥራ ኀላፊዎች ፤ የከፍተኛ ትምህርት የተማሪ ኅብረት ኀላፊዎችና ተጠሪ ተቋማት ተገኝተዋል።
Recent News
Follow Us