News Detail
Dec 27, 2025
33 views
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ቡኢ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ።
መርሃ ግብሩን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል(ዶ/ር) እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ አስጀምረውታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት በትምህርት ስርዓቱ የገጠመንን የሞራል ስብራት ለማስተካከል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ሀገር በፍጥነት ማደግ ከፈለግን በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት አለብን፤ በዚህም ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት በሀሉም አካባቢ ለመሥጠት በኢትዮጵያ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በርካታ ሀብት በማሰባሰብ የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገናና የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እስከዛው ድረስ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ የሆኑ የነገ ሀገር መሪዎችን ለማፍራት ከመላ ሀገሪቱ ተመርጠው የሚገቡባቸው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ትምህርት እያስጀመርን እንገኛለን ያሉ ሲሆን ።
ይህ ፕሮጀክት ወደፊት የሀገር መሪ የሚሆኑ ልጆችን ማፍራት አለብን በሚል የተቋቋመ በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ በቁርጠኝነት መሥራት አለበት ብለዋል።
ተማሪዎችም በአለም ተወዳድረን ከማንም ሀገር እኩል መሆናችንን ማሳየት የምንችለው በእናንተ ነው፤ ለዛም ነው ከሁሉም የሀገራችን ክፍል አወዳድረን በመቀበል ልዩ ትኩረት ሰጥተን እያስተማርናችሁ ያለው ያሉ ሲሆን ያገኛችሁት እድል ማንም ያላገኘው በመሆኑ ጠንክራችሁ ለተያዘው ራዕይ መሳካት መማር አለባችሁ ሲሉም አሳስበዋል።
አክለውም መምህራንና የትምህርት ቤቱ አስተዳደርም ከተማሪዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የመማር ማስተማር ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊና ልጆቹ ሰው ሆነው እንዲወጡ የማድረግ ጭምር በመሆኑ ይህንን ታሪካዊ ሀገራዊ ሀላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክንደያ ገ/ህይወት በበኩላቸው በእነዚህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ በመሆኑ ትርጉሙን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወደ አደጉት ሀገራት ደረጃ ለማሳደግ በእውቀት ብቻ ሳይሆን በስነ-ምግባር ፣ እርስ በርስ በመረዳዳት እንዲሁም ከማንም ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉ ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ጠንክረው መማር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) በትምህርት ዘርፉ እየተተገበሩ ባሉ የሪፎርም ተግባራት ውጤት ማየት ጀምረናል ያሉ ሲሆን ለዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት ሰኬታማነትም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
በመድረኩም ለልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ስልጠና ልምድ በመስጠት ድጋፍ ላደረገው የሀይሌ ማናስ አካዳሚ ምሰጋና ቀርቧል።