News Detail
Dec 25, 2025
55 views
የትምህርት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አዲስ ከተመደቡት የጣሊያን አምባሳደር ጋር ተወያዩ
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ አዲስ የተመደቡትን የጣሊያን አምባሳደር H.E. Sem Fabrizi በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ለረጅም ጊዜ የቆየ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ ግንኙነታቸው የበለጠ እየዳበረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በትምህርት ዘርፉ ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ ዋና ዋና የሪፎርም ተግባራትን ለአምባሳደሩ ያብራሩት ክቡር ሚኒስትሩ ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል የትምህርት ሥርዓት ለመዘርጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም ገልጸውላቸዋል።
በኢትዮጵያ አዲሱ የጣሊያን አምባሳደር H.E. Sem Fabrizi በበኩላቸው ጣሊያን በትምህርት ዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ስትሰራ መቆየቷን ጠቅሰው ይህንን ትብብር በማሻሻል ወደ ላቀ ደርጃ ማድረስ እንደሚፈልጉ ለክቡር ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በተለይም በአጠቃላይ ትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በኢትዮጵያና በጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚረግ ግንኙነትና በነጻ የትምህርት እድል ዙሪያ በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተማሪዎችና የመምህራን ልውውጥ እና የጋራ የምርምር ስራዎች ለመስራት ፣ የጋራ ዲግሪዎች የሚሰጡበት የትምህርት መርሃግብር ላይ ለመስማማት እና እንደ ኢራስመስ ፕላስ እና ሆራይዘን አውሮፓ ባሉ ዋና ዋና የጋራ ባለብዙ ወገን ፕሮግራሞች ውስጥ ትብብር ለማድረግ ተስማምተዋል።
በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በጣሊያን የትምህርት ሚኒስቴርና የብቃት ሚኒስቴር 'አንድ ላይ የማደግ ፕሮጀክት ውስጥ በሁለቱ ሀገራት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የትምህርት ተቋማት መካከል ትብብርና ልውውጥን ለማበረታታት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ እንዲዘጋጅ ከመግባባት ደርሰዋል።
Recent News
የትምህርት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ አዲስ ከተመደቡት የጣሊያን አምባሳደር ጋር ተወያዩ
Dec 25, 2025
የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተደረገላቸው አቀባበል
Dec 20, 2025
Dec 15, 2025