News Detail
Feb 28, 2026
29 views
በትምህርት ዘርፉ ሁሉም ዜጎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ገለፁ።
በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ አሞራቴ ከተማ የተገነባው የአሞራቴ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል፤ ተጨማሪ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት እቅድ ተይዟል።
በትምህርት ሚኒስቴርና በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገነባውን ትምህርት ቤት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ መርቀውታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት በትምህርት ዘርፉ ሁሉም ዜጎች አኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለማስቻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ዛሬ በዳሰነች የተመረቀው አዳሪ ትምህርት ቤት አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የራሱን ሥራ ሲሰራ ልጆቹ ተረጋግተው የሚማሩበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።
እነሱን ሳናስተምር ይች ሀገር ለሁላችንም እኩል ነች ማለት ከባድ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የዚህ ትምህርት ቤት መገንባት ትልቅ ደስታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በቀጣይ ምንም ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሌላቸው ወረዳዎችን በመለየት 1452 ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እየተሰራ ሲሆን በዳሰነችም ሁለት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገነባል ብለዋል።
መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጆች ከአምስት ዓመት ጀምሮ ለማስተማር በሰጠው ልዩ ትኩረት ባለፉት ዓመታት ከ34ሺ በላይ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል።
ይች ሀገር የተወሰኑ ሰዎች ሀገር ሳትሆን የሁሉም የኢትዮጵያውያን በመሆኗ የተረጋጋ ሀገር እንዲኖረን በትምህርት ዘርፉ ያለልዩነት እኩል ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው መንግስት በትምህርት ዘርፉ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለማስተካከል ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በተሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
ይህ ትምህርት ቤት ለዚህ አካባቢ ትርጉሙ ትልቅ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የተሻለ ነገ እንዲኖር ዛሬ የተሻለ ነገር እየሰራ ላለው ትምህርት ሚኒስቴር ምስጋና አቅርበዋል ።
የሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሰባስቲያን ብራዲስ በበኩላቸው ሰዎች ለሰዎች ከዚህ ቀደም በገነባቸው ትምህርት ቤቶች በርካታ ሙሁራን መውጣታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ትምህርት ቤትም ነገ ሀገር መምራት የሚችሉ ልጆች እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልፀው ትምህርት ቤቱ ዘላቂነት እንዲኖረው በባለቤትነት መንከባከብ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
Recent News
የአማሮ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።
Feb 27, 2026
አዲስ የተመደቡ የዩኒቨርስቲ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በትክክል እንዲወጡ ተጠየቀ ።
Feb 13, 2026