News Detail

National News
Feb 27, 2026 21 views

የአማሮ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ትምህርት ሚኒስቴር ከሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ያስገነባው የአማሮ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት ተመርቋል።
ትምህርት ቤቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ተገኝተው መርቀውታል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ዛሬ የተመረቀው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደ ሀገር ትምህርትን በፍትሃዊነት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ እንደ በፊቱ የመሠረት ድጋይ አስቀምጦ መሄድ ቀርቷል ያሉ ሲሆን በትምህርት ሴክተሩ ፕሮጀክት ጀምሮ በአጠረ ጊዜ መጨረስ ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ሴክተሩ ከፍተኛ የሞራል ውድቀት ውስጥ ወድቆ በመቆየቱ ከዚህ ለማላቀቅ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራት እየተተገበሩ መሆኑንና በተለይም ኩረጃን የሚጠየፍ በራሱ መስራትና መተማመን የሚችል ትውልድ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
አክለውም የትምህርት ስራ የሚለወጠው ከታች ጀምሮ ሲሰራ በመሆኑ በሁሉም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በዚህም ባለፉት አመታት ከ34ሺ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ 1452 ትምህርት ቤቶች በ726 ወረዳዎች በትምህርት ሚኒስቴርና በክልሎች ትብብር እንደሚገነቡ ጠቁመዋል ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ትምህርት ለሁለንተናዊ እድገትና ለዜጎች ከፍ ማለት ወሳኝ መሣሪያ በመሆኑ መንግስት በሪፎርሙ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የትምህርት ሴክተሩ እጅግ ስኬታማ ከሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑን አንስተው በተለይ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተገኘው ውጤት የሚደነቅ ነውም ብለዋል።
ይህ ትምህርት ቤትም ስታንዳርዱን ጠብቆ የተገነባ በመሆኑ ህብረተሰቡ በባለቤትነት ጠብቆ በመከባከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ሰባስቲያን ብራንስ በበኩላቸው ሰዎች ለሰዎች በትምህርት፣በጤና፣ በምግብ ዋስተናና በውሃ አቅርቦት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የዚህ ትምህርት ቤት መገንባት ሰፊ እድል ይዞ የመጣ በመሆኑ ውጤታማ ለመሆን ተማሪዎች ጠንክረው እንዲማሩም አሳስበዋል።
Recent News
Follow Us