News Detail

National News
Jan 28, 2026 32 views

ማህበረሰቡና አጋር የልማት ድርጅቶች የተቀናጀ ድጋፍ በትምህርት ዘርፉ የሚካሄደውን የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማ እያደረገው መሆኑ ተገለጸ።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ምቹ የመማሪያ አካባቢን ለመፍጠር ማህበረሰቡና የተለያዩ አጋር የልማት ድርጅቶት የሚያደርጉት ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ በትምህርት ስራው ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ሃላፊዎች ገለጹ።
በጋሞ ዞን ሠላም በር ከተማ አስተዳደር የሠላም በር 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መምህር የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ከማህበረሰቡና ከልማት ማህበራት የሚገኙ ድጋፎች የመማር ማስተማር ስራው ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም የማጠናከሪያ ትምህርት ለሚሰጡ መምህራን ማበረታቻ በመስጠት፣ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ የቤተ-ሙከራ ቁሳቁሶችን በማሟላት ረገድ ማህበረሰቡና በትምህርት ቤቱ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ልማት ማህበራት ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በስልጤ ዞን ስልጤ ወረዳ የሚገኘው አሳኖ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ዳይሬክተር አቶ ኑሪ ሸኩር በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች በማህበረሰቡና በአጋር የልማት ድርጅቶች ተሳትፎ እየተፈቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ ከማህበረሰቡ በሚያሰባስባቸው ድጋፎች አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ፣ የደንብ ልብስና የምግብ ድጋፍ በማድረግ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉና በተሻለ መልኩ ውጤታማ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል።
በትምህርት ዘርፉ ማህበረሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ለትውልድ ግንባታና የሚጠበቀውን የትምህርት ውጤት ለማስመዝገብ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ተብሏል።
Recent News
Follow Us