News Detail

National News
Dec 26, 2025 37 views

የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት አደረጉ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ ህይወት ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ቢሰራም ከትምህርት ጥራት አንፃር የትምህርት ሥርዓቱ ችግር ውስጥ ገብቶ ቆይቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ትምህርትና ፖለቲካ በመደበላለቃቸው የትምህርት ተቋማት የፖለቲካ ፍላጎት ማስጠበቂያ ተደርገው መቆየታቸውንም ሌላው ችግር መሆኑን አንስተዋል።
አሁን አለም እየሄደች ባለችበት መንገድ ተቋቁመን አብረን ለመቀጠልና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት በዚህ መንገድ መቀጠል ስለማይቻል ችግሩን ለመፍታት በትምህርት ዘርፉ በርካታ የሪፎርም ተግባራት ተቀርፀው እየተተገበሩ እንደሚገኝም አብራርተዋል ።
በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች እውነትና እውቀት የሚፈልቅባቸው በነፃነት ውይይት የሚደረግባቸው ዩኒቨርሳል ተቋማት መሆናቸውን ያነሱ ሲሆን፤
ዩኒቨርሲቲዎች ኢትዮጵያ ባላት ፀጋዎች ዙሪያ ትርጉም ያላቸው ፈጠራ እና ጥናትና ምርምር የሚደረግባቸው ተቋማት ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቅሰው ተቋማቱም ለስራዎቻቸው የሚበረታቱበት ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ አመራር ምደባም ከመንደር ወጥቶ በውድድር እንዲሆን እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ተግባራት ተቀርፀው እየተተገበሩ ሲሆን ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ አብዛኞቹን ወደ ፖሊሲና ውጤታማነት እየተቀየሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ከተመሠረተ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የተናሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ውጤታማ እንዲሆን የበለጠ ለጥራት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
Recent News
Follow Us