News Detail

National News
May 14, 2025 42 views

የትምህርት ሚኒስትሩ በአርሜንያ ሪፐብሊክ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባህልና ስፖርት ምክትል ሚኒስትር የተመራ ልዑካን ቡድንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአርሜንያ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባህልና ስፖርት ምክትል ሚኒስትር የተመራ ልዑካን ቡድንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና አርሜንያ ግንኙነት ታሪካዊ መሠረት ያለው መሆኑን በማንሳት በትምህርት ዘርፉ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፉ ጥልቅ ሪፎርም በማካሄድ የትምህርት ሥርዓቱን በመቀየር ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥኑ፣ ክህሎት ያላቸው፣ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት በርካታ ሥራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ለልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል።
በተለይም የትምህርት ሥርዓቱን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ለማላቀቅ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ረገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጀመር በቀጣይ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችንም ራስ ገዝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም በትምህርት ዘርፉ እየተወሰዱ ባሉ ሪፎርሞች ከሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውንም ለቡድን አባላቱ አብራርተዋል።
የአርሜንያ ሪፐብሊክ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባህልና ስፖርት ምክትል ሚኒስትር አርቱር ማርቲሮስያን በበኩላቸው አርሜንያና ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ይህንን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንፈልጋለን ብለዋል።
አክለውም በትምህርቱ ዘርፍ በከፍተኛ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርሲቲ ግንኙነት፣ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪግና ሂሳብ (STEM)፣ በጤና ትምህርት ፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዘርፍ በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርና ለአርሜንያ ስትራቴጂክ በመሆኗ ለምስራቅ አፍሪካ የትብብር ማዕከል ማድረግ እንፈልጋለን ያሉት ምክትል ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርት ዘርፉ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ አካላት በተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል፣ በምሁራንና አካዳሚክ ልውውጥ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ረገድ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ሰፊ ውይይቶችን አድርገዋል።
Recent News
Follow Us