News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jan 23, 2026 25 views

በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑ ተገልጸ።

በ2018 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትምህርት ቤቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ተገልጿል።
በተለይም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ታስቦ በመከናወን ላይ ያለውና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም አካባቢ እየተተገበረ ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት ተስፋ ሰጪ መሆኑም ተመላክቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘውና ባለውፈው ዓመት በአንጻራዊነት የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው የመቂቾ ሚሊኒየም 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ፈቱዲን ኑሪ እንደገለጹት ትምህርት ቤቱ በዚህ ዓመትም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከማሟላት ባለፈ፣ የጥናት ክፍለጊዜዎች በእቅድ እንዲመሩ በማድረግ ተማሪዎች በግቢ ውስጥ ቆይታቸው ትኩረታቸውን በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲሆን ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በተመሳሳይ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኘው የአለታ ወንዶ ህዳሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት ከተመዘገበባብቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ለውጤቱ መሳክት ጤናማ የሆነ የመማር ማስተማር ስርዓት መገንባቱ ዋነኛ ሚና እንደነበረው የትምህርት ቤቱ ር/መምህር አቶ ፍቅሬ ዳካ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከወላጆች በሚገኝ ድጋፍ ተማሪዎች በመረጡትና በሚያመቻቸው ጊዜ ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እና የመማር ማስተማር ስራው ያለምንም የጊዜ ብክነት እየተከናወነ በመሆኑ በተያዘው የትምህርት ዘመንም የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ ያላቸውን እምነት ርዕሰ መምህር አያይዘው ገልጸዋል።
መምህራን በበኩላቸው ከመደበኛው የመማር ማስተማር ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ በተቀመጠው የማጠናከሪያ ትምህርት መርሃ ግብር መሠረት ለተማሪዎች በተመረጡ የትምህርት አይነቶች ላይ ያተኮረ ልዩ ድጋፍ መስጠት፣ ያለፉ የብሔራዊ ፈተና ጥያቄዎችን የማለማመድ እና ተማሪዎችን በሥነ-ልቦና የማዘጋጀት ሥራ በመስራት ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ተማሪዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት የሁሉም ባለድርሻ አካለት ልፋት ድምር ውጤት በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበው ተማሪዎችም በኩረጃ የሚገኝ ነገር እንደሌለ አውቀው እየተቀየረ የሚመጣውን አለም መቋቋም የሚያስችለውን እውቀትና ክህሎት ለመጨበጥ አጥብቆ መማርና በትጋት ማጥናት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ልዩ ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳለ የሚታውስ ነው።
Recent News
Follow Us