News Detail
Dec 13, 2021
630 views
በአማራ ክልል የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዬን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
በትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራ ልዑክ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በአሸባሪው የህወሐት ቡድን የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ጎብኝተዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ የትምህርት ቤቶቹ መሰረተ ልማቶች መውደሙን፣ የመማሪያ ፕላዝማዎች መዘረፋቸውን፣ ኮምፒውተርና የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ ዘረፋና ውድመት እንደተፈጸመባቸው እና ትምህርት ቤቶችን በከባድ መሳሪያ መደብደባቸውን ተመልክቷል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማትን ከጎበኙ በኋላ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ትምህርት ቤቶችን ከመዝረፉ ባለፈ ድጋሚ አገልግሎት እንዳይሰጡ በማሰብ ማውደሙ የጨካኝነትና የክፋተኝነት ጥግ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሽብር ቡድኑ ዘረፋና ውድመት የተፈጸመባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ትምህርት ቤቶቹን ደረጃቸውን ባሟላ መልኩ እንደገና መልሶ ለማቋቋም የፌዴራልና የክልል መንግስት ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብረውና ተጋግዘው ትምህርት ቤቶቹን እንደሚገነቡም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማተብ ታፈረ ቡድኑ በአማራ ክልል ከአራት ሽህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ሙሉ በሙሉና በከፊል ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።
ከትምህርት ሚንስቴር ጋር በመተባበር መልሶ ግንባታዎች በአጭር ጊዜ እንደሚሰራም ቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
Recent News
Sep 02, 2025
Aug 29, 2025
Aug 28, 2025
Aug 23, 2025