News Detail
Jan 27, 2026
29 views
በ2018 አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በክልሉ ሁሉም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ እንደገለጹት በክልሉ በ2017 አገር አቀፍ ፈተና የተገኘውን ውጤት የበለጠ ከፍ ለማድረግ በሁሉም የክልሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባሉ በሁሉም የግልና የመንግስትም ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት በመፍጠር ተማሪዎችን በስነ ልቦና የማዘጋጀትና የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉን የቢሮ ኃላፊው አቶ ጌቱ ተናግረዋል።
በአደረጃጀቱ መሠረት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የተሻለ ልምድ ባላቸው መምህራን የማጠናሪያ ትምህርቱ እንዲሰጥ መደረጉን ገልጸው፤ ከመምህራን በተጨማሪም ጠንካራ ተማሪዎች ተመርጠው የሚረዳዱበት ፕሮግራም ተቀርዖ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ተማሪዎቹ ያላቸውን የጥናት ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉም ቤተ መጽሐፍቶች ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ከጠዋቱ 2:30 እስከ ምሽቱ 1:30 ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።
በዚህም ተማሪዎች ውጤት የሚገኘው ጠንክሮ በመስራት መሆኑን በመረዳትና ለትምህርታቸው ትኩረት በመስጠት የማንበብ ባህላቸው እየደገ መጥቷልም ብለዋል።
የቤተ ሙከራ አጠቃቀምን በሚመለከትም በተጠቀሱት ቀናት መምህራን ቤተ ሙከራዎችን ክፍት አድርገው ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙና እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ክልሉ ከታች ጀምሮ የትምህርት ጥራትን ለመረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በየደረጃው ትኩረት ሰጥቶ እየተገበረ እንዳለ የቢሮ ሃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።