News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Nov 07, 2025 49 views

በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራ የልዑካን ቡድን ከፊንላንድ የትምህርትና ባህል ሚኒስቴር ጋር ተወያየ።

(ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም) በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራ ልዑካን ቡድን በፊንላንድ እያደረ ካለው የልምድ ልውውጥ ጎን ለጎን ከፊንላንድ የትምህርትና ባህል ሚኒስቴር ጋር ተወያይቷል።

በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ በመምህራን ስልጠና ፣ በአካቶና በቅድመ ልጅነት ትምህርት ዙሪያ ከፊላንድ ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በአዲስ መልክ የተደራጀው የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲን በመምህራን ስልጠና ላይ ከሚሰሩ አቻ የፊንላንድ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በትብብር የሚሠሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ፍላጎት ያለ መሆኑን ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሳትፎና በትምህርት ቤት ምገባ ዙሪያ ላይ የማህበረሠቡን ተሳትፎ እና ድጋፍ ለማሳደግ በተሠሩ ስራዎች የገኙ አበረታች ውጤቶችን አስመልክቶ በክቡር ሚንስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ገለጻ ተደርጓል። 

የፊንላንድ ትምህርትና ባህል ሚኒስትር H.E Mr Anders E. Adlercreutz, በበኩላቸው ፊንላንድ የትምህርት ጥራት እና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የሄደችበትን ርቀትና የተገኙ ስኬቶችን አስመልክቶ ለልኡካን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል። 

ሁለቱም ሚኒስትሮች የመምህራን አቅም ማጎልበቻ ስራዎች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የተስማሙ ሲሆን የፊንላንድ ትምህርትና ባህል ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኩል ግብዣ ቀርቦላቸዋል።

በውይይቱ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወትና ሌሎች የዘርፉ አመራሮችም ተገኝተዋል።

Recent News
Follow Us