News Detail
Feb 08, 2026
45 views
የትምህርት ስርዓቱን በማጎልበት ሂደት ውስጥ የቴክኖሎጂ አቅምን አጠናክሮ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተገለፀ።
የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ምክክር የክልል ትምህርት ቢሮዎች ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተካሄ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን የትምህርት ዘርፉን በሚደግፍ አግባብ እና የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በሚያሳልጥ መልኩ የተጀመሩ ስራዎችን አስፍቶ የበለጠ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ አስገነዝበዋል።
ሚንስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የትምህርት መሰረተ ልማትን ከማስፋት አንጻር በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታና ዕድሳት በስፋት መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተማሪዎችን ከታች ቀርጾ ለማውጣት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት በመስጠት በስፋት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የምገባ መርሐ ግብርን በማጎልበት የተማሪዎችን የትምህርት ቅበላ አቅም የማሳደግና ስራዎች ተጠናክረው የቀጠሉ መሆኑን አብራርተዋል።
የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ወደ ተግባር መግባት ለትምህርት ጥራት የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ያሉ ሲሆን የመምህራንን እጥረት ለመቀነስ እና አቅማቸውን ለመገንባት ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውንም አያይዘው ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ113 ሺህ በላይ ለሆኑ መምህራን የክረምት ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና የተሰጠ መሆኑም ተያይዞ ተገልጿል።
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በትኩረት እየተተገበረ መሆኑንም አብራርተዋል።
የዚህ ምክክር መድረክ ዓላማም በክልሎች መካከል ተመሳሳይ አፈፃፀም እንዲኖርና የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥና በሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ የጋራ መፍትሄ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።