News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jun 05, 2025 128 views

በተለያዩ የትምህርት መስክ ሰልጥነው ወደ መምህርነት ሙያ መግባት ለሚፈልጉ አዲስ አማራጭ የአሠራር ሥርዓት ወደ ተግባር ሊገባ መሆኑ ተገለፀ። አዲስ በተዘጋጀው አማራጭ የመምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ ላይ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር በመምህርነት ሙያ የሚታየውን የሥልጠና እጥረት ለመቅረፍ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሰልጥነው የሚገኙና ወደ መምህርነት ሙያ መግባት ለሚፈልጉ አዲስ የአሠራር ሥርዓት ወደ ተግባር ሊያሰገባ መሆኑን በሚኒስቴሩ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ሀገራችን የመምህርነት ሙያ ማሰልጠን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለት ቢሆንም አማራጭ ወደ መምህርነት ለመግባት ለሚፈልጉት አዲስ መንገድ መክፈት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ተጨማሪ ሥልጠና ወስደው መምህር መሆን የሚችሉበት የሥልጠና ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በተለይም በትምህርት ዘርፉ ከተደረገው የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ ጋር አብሮ የሚሄድ ለደረጃው የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መምህራንን ለማፍራት የተለያዩ አማራጮች ተቀርፀው እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በዚህም መምህር ሆነው መሥራት ለሚፈልጉ ምሩቃን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ገብተው ተጨማሪ የመምህርነት ሙያ፣ የሚያስተምሩት ትምህርት አይነት ይዘት ፣ የትምህርት ቴክኖሎጂ እና የጋራ ኮርሶችን ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋልም ተብሏል።
የመምህራንና የትምህር አመራር ልማት ዴስክ ሃላፊ ወ/ሮ አሰገድ ምሬሳ በበኩላቸው የሀገራችንን የመምህራን አቅርቦት ለማሻሻል አማራጭ የስልጠና ሞዳሊቲዎች እየተጠኑ ወደ ስራ ማስገባት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በተደረገ የዳሰሳ ጥናት አብዛኞች በተለያዩ የትምህርት መስክ የተመረቁ ተጨማሪ የማስተማር ሙያ ስልጠና ቢሰጣቸው ወደ ሙያው የመግባት ፍላጎት እንዳለም ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የሥልጠና ማዕቀፉን ወደ ሥራ ለማስገባትም ከአሰልጣኝ የትምህርት ተቋማት፣ ከክልል ትምህርት ቢሮና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
አዲስ የተዘጋጀው አማራጭ መምህራን ማሰልጠኛ ማዕቀፍ ከቀጣይ ዓመት ጀሞሮ ወደ ተግባር ይገባልም ተብሏል።
Recent News
Follow Us