News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
May 30, 2025 67 views

ለትምህርት ቤቶች ግንባታ መሠረት ድጋይ አስቀምጦ መጥፋት ሳይሆን ቀጥታ ግንባታ በማስጀመር በአጭር ጊዜ አጠናቆ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ የሚያስችል ስልት ተቀይሶ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለፀ።

የትምህርት ሚኒስቴር በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ የሚያስገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀምሯል።
የትምህርት ቤቱን ግንባታ የትምህርት ሚኒስትሩና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በጋራ አስጀምረውታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ለትምህርት ቤቶች ግንባታ የመሰረት ድጋይ አስቀምጦ መጥፋት ሳይሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራን በማጠናቀቅ ግንባታዎችን በማስጀመር በተግባር በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
አክለውም ይህ ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ትምህርት ቤትም መሉ ወጪ በትምህርት ሚኒስቴር የሚሸፈን መሆኑን በመግለፅ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የመማር ማስተማር ሥራ ይጀምራል ብለዋል።
ሁሉም በሀገራችን የሚኖሩ ልጆች በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ ትምህርት፣ እውቀትና ክህሎት ማግኘት አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ አሁን ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች በፍተሃዊነትና በጥራት ለማድረስ የተጀመረው ሥራ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ አካባቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ ትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታም በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ያሉ ሲሆን ህብረተሰቡም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ እኩኝ ኡኬሎ በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ እንደ ሀገር በርካታ ትምህርት ቤቶች ቢገነቡም በክልሉ ያለውን ክፍተት በመለየትና ልዩ ትኩረት በመስጠት ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ግንባታው እስኪጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
Recent News
Follow Us