News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Oct 24, 2025 46 views

በትምህርት ቤቶችና አካባቢ የትምህርት አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ሰላማዊ መማር ማስተማርን በማስፈን ለተማሪዎች ውጤትና ሥነ-ምግባር መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ።

ትምህርት ቤቶችና አካባቢ የትምህርት አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ አግባብነት ካላቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የከፈቱት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ የትምህርት አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ ደንቡ ሰላማዊ መማር ማስተማርን በማስፈን ለተማሪዎች ውጤትና ሥነ-ምግባር መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያውኩ ጉዳዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው ይህንን ለማስተካከል ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ ዜጋ ማፍራት የደንቡ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ለተግባራዊነቱ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ መሥራት እንደሚጠበቅ ሚኒስትር ደኤታዋ አሳስበዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ እቶ ኡመር ኢማም በበኩላቸው ረቂቅ ደንቡን ለማዳበር በርካታ የውይይት መድረኮች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በየመድረኮቹ የሚነሱ ሀሳቦች በግብዓትነት ተወስደው ከተካተቱበት በኋላ ረቂቅ ደንቡ ሲጽድቅ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባለፈው ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ መውጣቱንና ይህም ደንብ አዋጁን ለማስፈጸም እየወጡ ካሉ የህግ ማዕቀፎች መካከል አንዱ መሆኑንም በመድረኩ ተጠቅሷል።
Recent News
Follow Us