News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Sep 07, 2025 25 views

ለሴት ተማሪዎች የትምህርት ውጤታማነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ገለፁ።

የጳጉሜን 2 የህብር ቀንን ምክንያት በማድረግ ለዳግማዊ ሚኒሊክ እና ለቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሴት ተማሪዎች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
በዚሁ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ የተደረገው ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ለሴት ተማሪዎች ትምህርት ውጤታማነት የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረው መሠል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
አክለውም በቅርቡ የጸደቀው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች አንዱ ሴት ተማሪዎችን በትምህርት ውጤታማ የማድረግ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ትምህርት ቤቶች ሴቶች በትምህርት ቤት ውስጥ ከሚያሰፈልጓቸው ነገሮች አንዱ የሆነውን የንጽህና መጠበቂያ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚደነግግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዋጁ በቅርቡ የጸደቀ መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለአዋጁ መተግበር በትምህርት ዙሪያ የሚሰሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው አገር የሚገነባው በእያንዳንዱ ዜጋ አስተዋጽኦ በመሆኑ በህብር በመቆም በአንድነት በመሆን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግና የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴቶቻችንን ማጎልበት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
አገር የሚለማው ሴቶችም ወንዶችም በህብር ቆመው በመሆኑ ለሴት ተማሪዎቹ የተደረገው ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ በሴት ልጆች ላይ ትልቅ ትርጉም የሚያመጣና ከትምህርት ገበታቸው የሚያስቀራቸውን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የ”ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ ለኢትዮጵያ” የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በዳግማዊ ሚኒሊክ እና እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያበረከተው እምዬ የተሠኘ በቴክኖሎጂ የታገዘ የንጽህና መጠበቂያ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ አግኝተው ትምህርታቸውን ያለ ችግር መቀጠል እንዲችሉ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ቴክኖሎጂውን ወደ ሌሎች ትምህርት ቤት የማስፋት ሥር እነደሚሰራም ተገልጿል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የህብር ቀንን በጋራ በማክበር ላይ ሚገኙ የሰባት ሚኒስቴር መ/ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ አጋር ድርጅቶችና የትምህርት ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል፡፡
Recent News
Follow Us