News Detail
Sep 18, 2025
29 views
የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ከተባበርን የትምህርት ዘርፉን ማሳደግ እንደምንችል ያሳየ ነው፤ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው “ትምህርት ለአገር ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የ2018 የትምህርት ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በተጠናቀቀው የ 2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት ነበር ብለዋል።
በተለይ በክልሉ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ለ12ኛ ክፍል ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች 22 በመቶ የሚሆኑትን ማሳለፍ መቻሉ በክልሉ የማንሰራራት ዘመን ጅማሮ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
ትምህርት አገራችንን ወደ ቀድሞ ታላቅነትና ገናናነት ክብር የሚያሻግር ነው ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የትምህርት ጥራት፣ተደራሽነትና ተሳትፎን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ስርዓቱ የነበሩ ስብራቶችን በመለየትና ስትራቴጂዎችን በማውጣት በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው ትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ትምህርት ቤቶች ምቹ እንዲሆኑ እያስቻለ ይገኛል ተብለዋል ።
ይህም ከተባበርን የትምህርት ዘርፉን ማሳደግ እንደምንችል ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ በክልሉ ለትምህርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመንም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በማስፈን የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በጉባኤውም በክልሉ እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህፃን ከትምህርት ገበታ እንዳይቀር ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል።