News Detail
Nov 22, 2025
41 views
የትምህርት ሚኒስትሩ በሲንጋፖር አምባሳደር የተመራ የልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋገሩ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሲንጋፖር አምባሳደርንና በሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጉዳይ ኃላፊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ጊዜ ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቱን በማሻሻል ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ለመስጠት እየወሰደቻቸው ያሉ የሪፎርም ተግባራትን ለልኡካን ቡድኑ ገልፀዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ በጀመረቻቸው አዳዲስ የልማት እቅዶች እንደ ፔትሮ ኬሚካል፣ ማዕድን ልማት፣ ቱሪዝም፣ ኒውክለር ሳይንስ እና በመሳሰሉት የትምህርት መስኮች ላይ በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳለ አንስተዋል።
የልዑካን ቡድኑን የመሩት አምባሳደር H.E Aselverjah በበኩላቸው ሲንጋፖር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ አጠናክራ በመቀጠል በቴክኖሎጂ ልውውጥ፣ በአቅም ግንባታ፣ በሥርዓተ ትምህርትና ነጻ የትምህርት እድል በመስጠት ረገድ በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
አያይዘውም በሲንጋፖር የትብብር ፕሮግራም የሰው ሃብት ልማት ፕሮጀክት እስከ አሁን 160 ሺህ በላይ የአፍሪካ ተማሪዎች በሲንጋፖር ዩኒቨርሲቲዎች መማራቸውና ከነዚህ ውስጥ 300 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
ይህንን ፕሮግራም በአሁኑ ሰዓት የበለጠ አጠናክረው በመቀጠል ኢትዮጵያ በምትፈልጋቸው የትምህርት መስኮች የነጻ የትምህርት እድል የመስጠት ፍላጎት ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ክቡር ሚኒስትሩም የሚሰጠው የነጻ የትምህርት እድል በኢትዮጵያ በማይሰጡና አዲስ ለተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ጠቃሚ በሆኑ የትምህርት መስኮች የተመረጡ ተማሪዎችን በመላክ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።