በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ያነጣጠረው አሉባልታ መሰረተ ቢስ ነው!

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የሰፈነበት ስኬታማ የትምህርት ዘመን እንዲሆን ከመላው የትምህርት ማህበረሰብ ጋር በመሆን በቁርጠኛነት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአዲስም ሆነ ለነባር ተማሪዎች በተለመደው ሁኔታ ትምህርት እየተሰጠ ቢሆንም ይህንኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማወክ አፍራሽ አሉባልታዎች በመሰራጨት ላይ መሆናቸውን መንግስት ደርሶበታል፡፡

በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞች የማጠናቀቂያ ጊዜ ላይ ‹‹መንግስት ለውጥ አድርጓል፤ጊዜውም ተራዝሟል›› የሚል ሀሰተኛ መረጃ ሃላፊነት በጎደላቸው ፀረ ሰላም ሃይሎች አማካኝነት እየተሰራጨ መሆኑ በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን  በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ቅር እንዳሰኘ ለማወቅ ተችሏል ፡፡

ምንም እንኳን በአንዳንድ አፍራሽ ሃይሎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን ላይ ያነጣጠረው ይህ  አሉባልታ መሰረተ ቢስ እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማወክ ያለመ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለውን ሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ ሊቀለብስ እንደማይችል መንግስት በፅኑ ያምናል፡፡

ስለዚህ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳይፈጥር በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚማሩ ተማሪዎች በየትኛውም የትምህርት ፕሮግራም  የተጨመረም ሆነ የተቀነሰ ዓመት የሌለ መሆኑን በማወቅ ትምህርታችሁን እንደ ወትሮው በተረጋጋ መንፈስ እንድትማሩ  እያሳወቅን ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት እንደ ወትሮው ሁሉ ለትምህርት መስፋፋት፣ፍትሃዊነት እና ጥራት መሻሻል የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያለውን ዕምነት ይገልፃል፡፡

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር