የትምህርት ቤት መሻሻል ዳይሬክቶሬት

ዳራ

የትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ ግብር በ1999 ዓ.ም. ተቀርፆ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ አንዱ መርሀ ግብር ሲሆን ቀደም ሲል የተጀመረውን የትምህርት ፕሮግራም በማጠናከር   የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር በትምህርት ቤት ደረጃ ለማሻሻል ራሱን ችሎ የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት በሚል ስያሜ  በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ተቋቁሟል፡፡

የትምህርት ቤት መሻሻል መርሃ ግብር ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ በተለያዩ የትምህርት ቤት ርዕሰ ጉዳዮች (Domains) አንፃር ግለ ግምገማ (self-evaluation) በማካሄድ የትምህርት ግብዓቱንና ሂደቱን በማሻሻል ተማሪዎች የላቀ የትምህርት ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ላይ ያተኮረ ፅንሰ ሀሳብ ነው።

የመርሃ-ግብሩ ዋና ግብ

የትምህርት ቤት መሻሻል ዋነኛ ግብ የተማሪዎችን ባህርይ እና የመማር ሁኔታ በማሻሻል የመማር ውጤታቸውን (Learning Outcome) በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ነው።

የትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ ግብር ርዕሰ ጉዳዮች (School domains)

 • መማርና ማስተማር፣
 • ምቹ የትምህርት ሁኔታና አካባቢ፣ 
 • የትምህርት ቤት አመራርና አስተዳደር እና
 • የህብረተሰብ ተሣትፎ ናቸው።

አደረጃጀት

ዳይሬክቶሬቱ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ሲገኝ በውስጡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራሞች አሉት። በዚሁ መሰረት አንድ ዳይሬክተር፣ 6 ባለሙያዎች (በእያንዳንዱ ፕሮግራም  ሁለት ሁለት ባለሙያዎች) እና 2 የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የተሰጠውን ተልእኮ በመወጣት ላይ ይገኛል።

የትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ ግብር ዋና ዋና ዋና ተግባራት

 • አገር አቀፍ የትምህርት ቤት መሻሻል ግቦችን መንደፍ፣
 • የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም አተገባበር ስልቶችን መቀየስ፣
 • በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ የትምህርት ቤት ማሻሻል ሥራዎችን ከታለመለት አጠቃላይ ግቦች አንፃር እየተካሄዱ መሆናቸውን መከታተል፣
 • በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ መመሪያዎችን፣ ማዕቀፎችን ስታንዳርዶችን ማዘጋጀት፣ ማስጠበቅ፣
 • ት/ቤቶች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልክ የቅድሚያ ትኩረት ጉዳዮችን በመለየት ስትራቴጅክ  እና አመታዊ እቅዶችን  በማዘጋጀት እና ስራ ላይ በማዋል ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ በድጋፍና ክትትል ማረጋገጥ፣
 • በትምህርት ቤቶች የትምህርት አመራር፣ አደረጃጀት፣ የህብረተሳሰብ ተሳትፎና የፋይናንስ መመሪያ ተግባራዊ  መደረጉን መከታተል፣
 • በአገር አቀፍ ደረጃ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራም ስታንዳርድ ደንብና መመሪያዎች ወዘተ… ማዘጋጀት ሥራ ላይ መዋላቸው መከታተል፣
 • በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤት መሻሻል ተግባራት በተማሪዎች የትምህርት ውጤት ላይ በተጨባጭ ያመጡትን ለውጦች ማጥናት/አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ ማስጠናት/፣ መገምገም፣ የመፍትሔ ሃሳቦችንም መጠቆም፣
 • በአገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ቤት መሻሻል  ሥራ ዙሪያ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ መረጃዎችን መስብሰብ፣ ማጠናቀር፣ መተንተን፣ መተርጐም፣
 • በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የትምህርት ግብአቶች በተማሪዎች ውጤት ላይና በትምህርቱ ጥራት ላይ ያስከተሉትን አንፃራዊ ተፅዕኖ በማጥናትና እንዲጠናም በማድረግ ለትምህርት ቤት መሻሻል ሥራ በሚኖራቸው ድርሻ ላይ ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዙ ጽሁፎችን ማዘጋጀት፣ ማስራጨት፣
 • በትምህርት ቤቶች የጤናና ስነ ምግብ ስትራቴጂ እና ማስተግበሪያ ሰነዶችን  መሰረት በማድረግ ስልጠናዎችን መስጠት፣ አፈፃጸሙን መከታተልና ድጋፍ መስጠት፣
 • የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም አፈፃፀም ብቃት ለማሳደግ በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ፈጻሚዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት፣
 • ት/ቤቶች ለእቅዶቻቸው ማስፈፀሚያ የሚሆን ሀብት በማፈላለግ እና የተገኘውን ሀብት  ለት/ቤቶች በማከፋፈል ስራ ላይ መዋሉን በድጋፍና ክትትል ማረጋገጥ፣
 • በት/ቤቶች የውሀ፣ የንፅህና እና የጤና ( WASH) መርሀ ግብር ትግበባራዊነትን መከታተልና መደገፍ፣
 • የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም አተገባበርን መከታተል እና ድጋፍ መስጠት፣

ከምስረታ ጀምሮ እስከ 2008 የተገኙ ዋና ዋና ውጤቶች

 • የወመህ/ወተመህ እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት መድረኮችን በማካሄድ የማህበረሰቡ እና የትምህርት ቤቶች ግንኙነት ተጠናክሯል።
 • የትምህርት ቤት ድጎማ በጀት ለትምህርት ቤቶች መሻሻል መርሀ ግብር ዕቅድ ማስፈፀሚያ እንዲውል ተደርጓል።
 • ሁሉም ት/ቤቶችእና 98% የሚሆኑት የአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ጣቢያዎች ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የ3 ዓመትስትራቴጂክ እና ዓመታዊ እቅድ በማዘጋጀት ተግባራዊ አድርገዋል።
 • ሀገር ዓቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ አተገባባር ስትራቴጂ (ረቂቅ ሰነድ) በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተዘጋጅቷል።
 • በኢሊኖ ክስተት ምክንያት በተፈጠረው ድርቅ ችግሩ በተባባሰባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ት/ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች ከመንግስት በጀት እንዲመደብ በማድረግ ትምህርታቸውን ተረጋግተው መማር የሚያስችላቸውን የትምህርት መሳሪያዎች እና የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ ተደርጓል። 

በሁለተኛው እድገትናትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ የተቀመጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች

 • በትምህርት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ፣
 • የትምህርት ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻልና ግብዐት በማሟላት የትምህርት ቤት አካባቢን ምቹ ማድረግ፣
 • የመማር-ማስተማር ሂደቱን ለማሻሻል የአቻ ለአቻ ድጋፍን እና የርስ በርስ ትስስርን በማሳደግ፣ የተከታታይ የሙያ ማሻሻያ መርሀግብርን ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም የትምህርት ቤት የጉድኝት ማእከላትን ትስስርን ማጠናከር፤

የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ማስተግበሪያ ሰነዶችና የህትመት ውጤቶች

 • የትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ ግብር ማዕቀፍ፣
 • የትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ ግብር አተገባበር ገዥ መመሪያ፣
 • የአማራጭ መሰረታዊ ትምህርት ጣቢያዎች መሻሻል መርሀ ግብር መመሪያና ማዕቀፍ
 • የቀዳማይ ልጅነት ዘመን እንክብካቤና ትምህርት በኢትዮጵያ - ብሄራዊ ፖሊሲ ማዕቅፍ ( የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ ቅጂዎች)
 • የቀዳማይ ልጅነት ዘመን እንክብካቤና ትምህርት በኢትዮጵያ - ስትራቴጂካዊ የትግበራ ዕቅድና መመሪያ በኢትዮጵያ ( የአማርኛ አና የእንግሊዘኛ ቅጂዎች)
 • An Evaluation of the Child-to-Child School Readiness Program in Ethiopia.
 • Manual for training parents to enhance early child development.
 • በሁለተኛው ምዕራፍ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የትምህርት ቤቶች ድጎማ በጀት መመሪያ ( የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ ቅጂዎች)
 • የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ት/ቤቶች በየአመቱ የተቀመሩ የምርጥ ተሞክሮ ሰነዶች፣
 • የቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ስታንዳርድ፣

Address Address

Directorates and Departments Directorates and Departments