የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት

ዳራ

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት መጀመርን ተከትሎ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥተውት የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ዝግጅትንና ሌሎችንም ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል። በአዲሱ መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (BPR) ጥናት መሠረት ከሚያዝያ 2001 ዓ.ም ጀምሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ አንኳር የሥራ ሂደት በሚል ስያሜ ተዋቅሮ ዳይሬክቶሬቱ ተመስርቶ ነበር። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ ተደርጓል።  

 

አደረጃጀት

የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት በትምህርት ሚኒስቴር በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ውስጥ ከሚገኙት የሥራ ክፍሎች መካከል አንዱ ነው።ዳይሬክቶሬቱ በአንድ ዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን በእያንዳንዱ የትምህርት ዓይነት የተመደቡ 19 ባለሙያዎችና ሁለት የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች (አንድ ጸሐፊና አንድ የመልዕክት ሠራተኛ) አሉት። በዚህ አደረጃጀት የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ ቢሆንም ከአሁኑ በተሻለ ደረጃ እንዲገኝ በኢንስቲትዩት ደረጃ ለማደራጀት ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል።

 

ግቦች

•  በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች 75% እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ተማሪዎችን ማፍራት

•  ውጤታማ ሥራን ሊሠራና ሥራ ፈጣሪም መሆን የቻለ፤ በደረጃው በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የሆነ፤ በመልካም የዜግነትና የሥነምግባር ዕሴቶች የታነፀና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁለንተናዊ ልማትና ፈጣን ዕድገት ጉልህ አስተዋፅዖ ሊያደርግ የሚችል ዜጋ ማፍራት

 

ዓላማዎች

 • የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መሠረት ያደረገ እና ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረፅ የመማር ማስተማሩን ክንውን ስኬታማ ማድረግ፣
 • መልካም አስተዳደራዊና ዲሞክራሲ በሰፈነበትና ተማሪን ማዕከል ባደረገ የትምህርት አሰጣጥ ውጤታማነትን ማጎልበት፣

 

ዋና ዋና ተግባራት

 • በመመሪያው መሠረት የትምህርት/የሥልጠና መስክ የባለድርሻ አካላት ፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣
 • ከተለያዩ ሀገራት/ተቋማት መሠረታዊ የሥርዓተ ትምህርት ማቴሪያሎች አዘገጃጀት ዓለም አቀፍ ልምድ መውሰድና የተለያዩ አማራጭ መሠረታዊ የሥርዓት ትምህርት ማቴሪያሎች መቅረጽ/ማዘጋጀት
 • ተስማሚ የሥርዓተ ትምህርት ማቴሪያሎችን በባለሙያዎች ማስገምግም፣ መምረጥ፣ ማጣጣም፣
 • መሠረታዊ የሥርዓተ ትምህርት ማቴሪያሎች ማሳተምና ማሠራጨት፣
 • በየትምህርት ዓይነቱና ክፍል ደረጃው የተዘጋጁ የሙሉ ወይም የተወሰኑ ገጾች መ/ማ ማቴሪያሎች (ሀርድና ሶት ኮፒ) ናሙናዎችን ማወዳደር፣ መምረጥና ማጸደቅ፣
 • ለመምህራን ሥርዓተ ትምህርቱንና የመማሪያ ማስተማሪያ ማቴሪያሎችን ማስተዋወቅ
 • ተከታታይና አጠቃላይ ግምገማዎች በማከናወን የሥርዓተ ትምህርቱን አተገባበር መፈተሸ፣ ማሻሻል፤ መከለስናአስፈላጊ ሲሆን መለወጥ

 

በ2008 ዓ.ም የተገኙ ስኬቶች

የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት፣ ህትመት፣ ዳግም ህትመትና ሥርጭትን በተመለከተ የሁለተኛ ደረጃ 6.9 ሚሊየን የሚጠጉ ቅጂዎች ታትመው ለክልሎች የተሰራጩ ሲሆን ለአንደኛ ደረጃ 30.1 ሚሊየን ቅጂዎች ታትመው በስርጭት ላይ ይገኛሉ። 

 

በ7 የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሲዳሞ አፎ፣ ወላይታቶ፣ ሀዲይሳ እና በአፍ ሶማሌ፡ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት የተዘጋጀ ሲሆን ከ3ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ላሉት ወደ 5.5  ሚሊየን የሚጠጉ ቅጂዎች ታትመው ለክልሎች ተሰራጭተዋል። ቀሪዎቹ 16.8 ሚሊየን የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ህትመታቸው ተጠናቆ በመሰራጨት ላይ ይገኛሉ። የመጻሕፍት ስርጭቱ እጥረት በመቅረፍና የተማሪ መጻሕፍት ጥምርታን 1:1 በማድረስ የመማር ማስተማሩን ስራ ውጤታማ ያደርገዋል።

 

ቅድመ መደበኛ ትምህርትን በተመለከተ፡ ለተፋጠነ የትምህርት ቤት ዝግጁነት ፕሮግራም  የሥርዓተ ትምህርት ሰነዶችና የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ተዘጋጅተውና  በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተሞክረው ውጤታማነታቸው በጥናት ተረጋግጧል ። ለኦ ክፍል ሕፃናት አገልግሎት የሚውሉ  ደጋፊ  መጻሕፍት በቅድመ ቋንቋ፣ በቅደመ ሒሳብና በአካባቢ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች ተዘጋጅተው ክልሎች ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉመው  መጠቀም እንዲችሉ  ተሰራጭተዋል።

 

የልዩ ፍላጎት ትምህርትን በተመለከተ፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ለሚማሩ መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች በምልክት ቋንቋ እንዲማሩ ለማስቻል 16 የመማሪያ ማስተማሪያ  መጻሕፍትና  የኦቲዝም ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የማስተማሪያ የመምህር ማኑዋል ተዘጋጅተው ክልሎችና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የማስማማት ስራ በማከናወን ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉመው እንዲጠቀሙባቸው ተሰራጭተዋል።

 

አጋዥ መጻሕፍት፣ ማኑዋሎችና ስታንዳርዶች ዝግጅትን በተመለከተ፡ የህፃናትን የንባብና የጽሁፍ ክሂል ለማሻሻል የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት  ከማዘጋጀት በተጨማሪ  ከ1ኛ-4ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ህፃናት በ7ቱ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎችና በሒሳብና በአካባቢ ሳይንስ አጋዥ (supplementary) መጻሕፍትን በ31 ሚሊየን ቅጂዎች  ተዘጋጅተው ታትመው ለስርጭት ተዘጋጅተዋል። በሒሳብና በሳይንስ ትምህርቶች  በታችኛው ክፍል ደረጃ ክብደት ያላቸውን ፅንሰ ሃሳቦችና ይዘቶች በማብራራትና በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች የነበሩ ዝቅተኛ የተማሪዎች ውጤቶችን በማሻሻል ረገድ ፋይዳ ይኖራቸዋል። ለ9ኛና 10ኛ ክፍሎች የጂኦግራፊ መምህራን የሚያገለግል  የማፕሪዲንግ ማኑዋል በ10,000 ኮፒ ታትሞ  ለክልሎች ተሰራጭቷል።

 

የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት መርሀ ግብርን በተመለከተ፡ ከ5ኛ-8ኛ ክፍል በ11ዱ እሴቶች ላይ በአማርኛ፣ በሶማልኛና በእንግሊዝኛ የተዘጋጁትን የሥነዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት አጋዥ መጻሕፍት ለታዳጊ ክልሎች በ42,000 ኮፒ ታትሞ  ተሰራጭቷል፡፡

 

የሞራልና የሃይማኖት መቻቻልን በሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች 12ኛ ምዕራፍ ሆኖ ተካቶ እንዲሰጥ የተዘጋጀው እሴት በ2009 የትምህርት ዘመን ወደ ትግበራ ይገባል። የሰላም ትምህርት ይዘቶችን ከ1ኛ-4ኛ ክፍል ከአካባቢ ሳይንስ ጋር እንዲሁም ከ5ኛ-12ኛ ክፍል   ከሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ጋር  አዋህዶ ለማዘጋጀት ስራው ተጀምሯል።

 

በአምሰተኛው የትምህርት ልማት መርሐግብር (ESDP-V) የዳይሬክቶሬቱ የትኩረት አቅጣጫዎች

 • የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬትን ወደ ሥርዓተ ትምህርት ተቋም (Institute of Curriculum) ማሳደግ፣
 • በሚከለሰው ሥርዓተ ትምህርት ከkG-12 ክፍል በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የሥራ ፈጠራንና የቴክኒክና ሙያ ይዘቶችን በሚፈለገው መጠን በማካተት መከለስ፣
 • በሁሉም የትምህርት እርከኖች የሁሉም የትምህርት አይነቶች በተከለሰው ሥርዓት ትምህርት መሠረት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት መጀመር
 • በሁሉም የትምህርት እርከኖች የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የመማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍት  ዳግም ህትመት ማከናወን፣
 • የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክን በሚዛናዊነት ያካተተ  የታሪክ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት ከ9ኛ እስክ 12ኛ ክፍል ማዘጋጀት፣
 • ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት የግብረገብ፣ የሀገር ፍቅር፣ ተከባብሮ በሰላም የመኖርና የእኩልነት ይዘቶች እንዲሁም በየትምህርት ዓይነቱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የጥሩ ስብእና ግንባታ ይዘቶችን በሚፈለገው መጠን ማካተት፣
 • ለልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች አስፈላጊ የሆኑ የመማሪያና ማስተማሪያ መጻሕፍት ማዘጋጀት፣
 • የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት በተማሪዎች ባህሪ ላይ ያሰገኘውን ለውጥ በየትምህርት እርከኑ ለማወቅ ጥናት ማካሄድ።
 • ተዘጋጅተውና ታትመው የሚሰራጩ የመማረያ ማስተማሪያ  መጻሕፍትን  ስርጭት ለመከታተል  የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣
 • የንባብና የሒሳብ ክሂልን ለማጠናከር  የሚረዱ አጋዥ ማቴሪያሎችን እንዲሁም አጋዥ/ደጋፊ መጻሕፍትንና ማኑዋሎችን በማዘጋጀትና በማሳተም  ማሰራጨት፣
 • የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ሰነዶችና ማስተማሪያ ስልቶች አተገባበር ላይ ጥናትና ምርምር  ማድረግ፣
 • የቅድመ መደበኛ ትምህርት ላላገኙ ህጻናት በተለያዩ ዘዴዎች (Modalities) የሥርዓተ ትምህርት ሰነዶችን ማዘጋጀት፣
 • የሰላም ግንባታ ትምህርት(Peace Building Education) በሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ውስጥ ማካተት፣
 • ለሁሉም የክፍል ደረጃዎችና የትምህርት አይነቶች  ሥርዓተ ትምህርቶች   የተከታታይ  ምዘና   ስልቶችን  በክፍል ውስጥ እንዲተገበሩ ማኑዋሎች ማዘጋጀትና ለመምህራን ስልጠና  መስጠት፣

Address Address

ስልክ: +251 11 1564046 ፋክስ: +251 11 580937   ኢሜል: curri@moe.gov.et 

Directorates and Departments Directorates and Departments