የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ

ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የተመዘገቡትን ውጤቶቻችን ቀጣይነት ለማረጋገጥና የበለጠ ውጤት በማስመዝገብ ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ተጠናቆ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለተኛ አመት ላይ እንገኛለን፡፡ እተመዘገበ ያለውን ፈጣን ልማት ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማስቀጠል እና አገራዊ ራዕያችንን እውን ለማድረግ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የትምህርት ሴክተሩ የማይተካ ድርሻ እንዳለው በሃገር ደረጃ ግንዛቤ የተያዘበት ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ  የሰው ሀብታችንን አቅም ለማሳደግ፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በአስተማማኝ የሰፈነባትን ሀገር ለመገንባት የተያያዝነውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ  የትምህርት ሴክተሩ ሚና በጥቅሉ፣ በተለይ ደግሞ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።

 

በሚኒስቴር ዴኤታ የሚመራው የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ መሰናዶ (12 ክፍል) ድረስ ያሉትን የትምህርት ደረጃዎች ያጠቃልላል፡፡ በዚህ ውስጥም የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጐልማሶች እንዲሁም መደበኛ ያልሆነ ትምህርት ይካተታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ስርዓት አወቃቀር መሰረት በመጀመሪያ የምናገኘው የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ሲሆን ይንም አፀደ-ህፃናትን በሶስት ደረጃ በመከፋፈል ወይም በእንግሊዘኛ በተለምዶ አጠራራቸው ነርሰሪ ኪንደርጋርተን እና ፕሬፓራቶሪ የያዘ ሲሆን የሚጠናቀቀውም ሀጻናቱ ወደ አንደኛ ክፍል ሲዛወሩ ይሆናል፡፡

 

በመቀጠልም በመደበኛ ትምህርት የመጀመርያ ደረጃ አንደኛ ሳይክል የምናገኝ ሲሆን ይህም ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍሎች  ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ ከነዚህ ጋር ትይዩ በሆነ መልኩ አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት የሚገኝ ሲሆን ይህም ከአንድ እስከ አራት ደረጃዎች አሉት፡፡

 

ቀጣዩ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሣይክል ሲሆን ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍሎች ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ የአማራጭ መሠረታዊ ትምህርት 4 ደረጃን ያጠናቀቁ ተማሪዎች በመደበኛው አምስተኛ ክፍል ገብተው መቀጠል ይችላሉ፡፡

 

ተማሪዎች 8 ክፍልን ሲያጠናቅቁ የመጀመሪያ ደረጃ መልቀቅያ ፈተናን በመወሰድ የሚያልፉት ወደ ሁለተኛ ደረጃ አንደኛ ሳይክል በመግባት 9ኛና 10 ትምህርትቸውን ይቀጥላሉ፡፡ አዚህ ላይ ከአስረኛ ክፍል በታች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች መደበኛ ባልሆነ የማንበብና የመጻፍ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ መቀጠል ይችላሉ፡፡

 

የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን 10 ክፍል ማጠናቀቂያ ላይ በመውሰድ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት የሚያልፉት ተማሪዎች 11 እና 12 ክፍል ትምህርትን ይከታተላሉ፡፡ ሲያጠናቅቁም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን በመውሰድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመቀበል አቅም በሚወሰነው የመግቢያ ነጥብ መሰረት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመግባት ትምህርታቸውን በዲፕሎም በቢኤ በማስተረስ እና በፒኤችዲ ደረጃ በሚመርጡት መስክ ትምህርታቸውን መከረታተል ይችላሉ፡፡