ስልጣንና ተግባር ስልጣንና ተግባር

የትምህርት ሚኒስቴር በኢትዮዽያ ፌደራላዊ ዲሞከራሲያዊ ሪፐብሊክ የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በህገመንግስት አንቀፅ ፶፭ (፩) መሰረት የወጣው አዋጅ ቁጥር ፱፻፲፮/፪ሺ፰ የትምህርት ሚኒስቴር የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት እንደሚኖሩት ይዘረዝራል ፡-

 1. የትምህርትና ሥልጠና ስታንዳርድ ያወጣል፤ በሥራ ላይ መዋሉንም ያረጋግጣል፤
 2. የንዑስ አንቀጽ (1) አጠቃላይ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ፡-
  • ሀ) ሀገራዊ የብቃት ማዕቀፍ ያዘጋጃል፤
  • ለ) አጠቃላይ የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ያዘጋጃል፤
  • ሐ) የመምህራንን አነስተኛውን የትምህርት ብቃት መለኪያ ያወጣል፤
  • መ) የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ሊያሟሉ የሚገባቸውን አነስተኛውን ደረጃ ያወጣል፤
 3. የከፍተኛ ትምህርት እንዲስፋፋ ያደርጋል፣ በበላይነት ይመራል፤
 4. በየደረጃው ባሉ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርትና ሥልጠና መሰጠቱን ያረጋግጣል፤
 5. የሀገሪቱን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲና ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ያደረጉ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ያዘጋጃል፣ ያስተዳድራል፤ የውጤት ሪከርዶች ይይዛል፣ የውጤት, ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ይሰጣል፤
 6. የሀገሪቱን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ስትራቴጂን ይቀርጻል፤ በሥራ ላይ መዋሉን ያረጋግጣል፤
 7. የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላና ምደባ አፈጻጸም ፍትሃዊ መሆኑን ያረጋግጣል፤
 8. ትምህርትና ሥልጠናን በተመለከተ ሀገራዊ የአህዝቦት ተግባሮችን ያከናውናል፡፡
 9. በሥራው መስክ፡-
  • ሀ) ፖሊሲዎችንና ሕጎችን ያመነጫል፣ዕቅድና በጀት ያዘጋጃል፣ሲፈቀድም በሥራ ላይ ያውላል፤
  • ለ) የፌደራል መንግሥቱ ሕጎች በሥራ ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣል፤
  • ሐ) የጥናትና ምርምር ተግባሮችን ያከናውናል፣ መረጃዎችንይሰበስባል፣ያቀነባብራል፣ያሰራጫል፤
  • መ) የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ያከናውናል፣ የለውጥና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይፈጽማል፣ ያስፈጽማል፣ ዉጤታማነታቸውን ያረጋግጣል፤
  • ሠ) ለክልሎች እንዳስፈላጊነቱ ድጋፍና ምክር ይሰጣል፤ እንዲሁም ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ክልሎች በፌደራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተቀናጀ ድጋፍ ያደርጋል፤
  • ረ) በሕግ መሠረት ውሎችንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ያደርጋል፤
 10. በማቋቋሚያ ሕጎቻቸው ወይም በዚህ አዋጅ አንቀጽ 38 ተጠሪ የተደረጉለትን አስፈጻሚ አካላት አፈጻጸም በበላይነት ይመራል፤ያስተባብራል፤ አደረጃጀቶቻቸውን እንዲሁም የሥራ ፕሮግራሞቻቸውንና በጀቶቻቸውን መርምሮ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲቀርቡ ይወስናል፤
 11. የሚያዘጋጃቸው ፖሊሲዎች፣ሕጎች፣ የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች የሴቶችንና የወጣቶችን ጉዳይ እንዲያካትቱ መደረጋቸውን ያረጋግጣል፤
 12. የአካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ የማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እና በደማቸው ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች በኃላፊነቱ ክልል የእኩል ዕድል ተጠቃሚና ሙሉ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
 13. በዚህ አዋጅና በሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባሮች በሥራ ላይ ያውላል፤
 14. አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከሥልጣንና ተግባሩ በከፊል ለሌላ የፌደራል ወይም የክልል አካል በውክልና ሊሰጥ ይችላል፤
 15. ስለሥራው ክንዋኔ በየወቅቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል፡፡

ስለ ትምህርት ሚ/ር ስለ ትምህርት ሚ/ር