ዳራ

የህግ አገልግሎት ክፍል ተቋማችን በ1935 ዓ.ም የትምህርትና የሥነጥበብ ሚኒስቴር ተብሎ በንጉሱ ትዕዛዝ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተቋሙ የአስተዳደር አካል በመሆን ተቋቁሞ ያለና በ2002 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ተግባራዊ በተደረገው የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ጥናት መሠረት በድጋሚ ተቋቁሞ አገልግሎት እየሠጠ ያለ ክፍል ነው።

የህግ አገልግሎት ክፍሉ ዋና ዋና ግቦች

 • የተቋሙ አሠራር ህግና ሥርዐትን የተከተለ እንዲሆን ማስቻል፣
 • የህግ   ሠነዶች ህጋዊ ቅርጽና ይዘት እንዲኖራቸው ማስቻል፣
 • ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም በሥሩ ያሉ ዳይሬክቶሬቶች ባከናወናቸው ህጋውያን ተግባራት ሣቢያ በተቋሙ ስም በሚከስበትም ሆነ በሚከሰስበት ጊዜ ተቋሙን ወክሎ በውሣኔ ሰጭ አካላት ዘንድ በመቅረብ የተቋሙን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ የክፍሉ  ዋና ዋና ግቦች ናቸው።

የህግ አገልግሎት ክፍል አደረጃጀት

የአገልግሎት ክፍሉ በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና የድጋፍ ሰጭ ዘርፍ ሥር ከሚገኙ የሥራ ክፍሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን የክፍሉን ኃላፊ ጨምሮ ፣ የህግ ምክርና አስታያየት እንዲሁም የሰነድ ዝግጅት ባለሙያ ፣ የፍርድ ቤት ጉዳዩች ክትትል ባለሙያዎች፣ ጉዳይ አስፈፃሚ፣ ሴክሪታሪ፣ የመልክት ሠራተኛ በድምሩ በ7 የሰው ሀይል ተደራጅቶ ሥራውን በማከናውን ላይ የሚገኝ ሲሆን እንደአስፈላጊነቱ በውጭ ባለሙያ ጭምር በመታገዝ አገልግሎት በመስጠት ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል።

የህግ አገልግሎት ክፍል ዋና ዋና ተግባራት

 • ከህግ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ሲጠየቅ በፁሁፍና በቃል የምክር አገልግሎት መስጠት፣
 • የተቋሙ የአስተዳደር ክፍሎችና ውሣኔ ሠጭ አካላት የሚያስተላልፋቸው ውሣኔዎች የአገሪቱን ህገመንግስት፣ ዝርዝር ህጐች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በጠበቀ መንገድ መሆኑን ያረጋግጣል፣
 • በህጋዊያን ተግባራት ላይ ሲጠየቅ የውሣኔ ሀሣብና አስተያየት ይሰጣል፣
 • በተቋሙ የሚዘጋጅ ረቂቅ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተገቢው ህጋዊ ቅርፅ እንዲኖራቸው በማድረግና ታይቶ እንዲፀድቅ አግባብነት ላለው አካል ያስተላልፋል፣
 • ተቋሙ ከሣሽም ሆነ ተከሣሽ በወሆነባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዮች በመደበኛ ፍ/ቤቶች እንዲሁም በግልግል ተቋማት በመገኘት ተገቢውን ክርክር በማድረግ የተቋሙን መብትና ጥቅም ያስጠብቃል፣
በአገልግሎት ክፍሉ በተከናወኑ ተግባራት እስከ 2008የበጀት ዓመት የተገኙ ዋና ዋና ውጤቶች፣
 • በተቋሙ ውስጥ ከሚገኙ የሥራ ክፍሎች ለቀረቡና በቁጥር 70 ለሆኑ ጉዳዮች አስተያየትና የህግ ምክር አገልግሎት መሰጠት የተቻለ ሲሆን ይህም ተቋሙ ተግባሩን በህግ መሠረት እንዲያከናውን አስችሏል።
 • በሥራ ክፍሉ ለሥራ የቀረቡት ጉዳዮች የያዙት የገንዘብ መጠን 37,398,162.24 /ሰላሣ ሰባት ሚሊዩን ሶስት መቶ ዘጠና ስምንት ሺህ አንድ መቶ ስልሣ ሁለት ብር ከሃያ አራት ሣንቲም ሲሆን በአጠቃላይ ተቋሙ ከሳሽና ተከሣሽ ከሆነባቸው 31 መዝገቦች 21,632,530.76 /ሃያ አንድ ሚሊየን ስድስት መቶ ስልሣ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ሰላሣ ብር ከሰባ ስድስት ሣንቲም/ የሆነ ገንዘብ በማስፈረድ ሚኒስቴር መ/ቤቱ መብትና ጥቅሙ የተጠበቀ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ ተችሏል።
 • በአንድ አዋጅ በአንድ ደንብና በአንድ መመሪያ ረቂቅ ዝግጅት ላይ በማሳተፍና ህጋዊ ቅርፅ በማስያዝ አግባብነት ላላቸው አካላት በመላክ እንዲፀድቁ የተደረገ ሲሆን የከፊሎቹን መፅደቅ በመከታተል ላይ ይገኛል።

በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ የተቀመጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች

ከአገልግሎቱ የሥራ ባህሪ አንፃር የእድገትና የትራስፎርሜሽን እቅድ በግልፅ ያስቀመጠው የትኩረት አቅጣጫ ባይኖርም እቅዱን ለማስፈፀም ርብርብ የሚያደርጉ አላማ ፈፃሚ የሥራ ክፍሎችን የመደገፍ ሚናውን በላቀ ደረጃ ለመውጣት እቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል።

የህግ አገልግሎት የሥራ ማከናወኛ ሰነዶችና የህትመት ውጤቶች

 • የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገመንግሥት
 • የፍትሐብሔር ህግ
 • የወንጀለኛ  ህግ
 • የንግድ ህግ
 • የአገር አቀፍ የትምህርት ፖሊሲ
 • በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል በተለያየ ጊዜ የወጡ ህጐች
 • በሚኒስትሮች ም/ቤት በተለያዩ ጊዜ የወጡ ደንቦች
 • እንዲሁም ተቋሙ አዋጆች ደንቦችን ለማስፈፀም ያወጣቸው መመሪያዎች ክፍሉ ሥራውን ለማከናወን የሚጠቀምባቸው ሰነዶች ናቸው።

ዳይሬክቶሬቶች እና የስራ ክፍሎች ዳይሬክቶሬቶች እና የስራ ክፍሎች