በሂሳብና ሳይንስ የትምህርት አይነቶች ለ544 አሰልጣኞች የተግባር ስልጠና ተሰጠ

በሂሳብና ሳይንስ የትምህርት አይነቶች ለ544 አሰልጣኞች የተግባር ስልጠና ተሰጠ

በግማሽ አመቱ 544 በሂሳብና ሳይንስ የትምህርት አይነቶች ክልላዊ አሰልጣኞችን የተግባር ስልጠና ማሰልጠን መቻሉን በትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማእከል አስታወቀ፡፡

ማእከሉ የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት የማእከሉ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ በላይነህ ተፈራ በግማሽ አመቱ 560 ክልላዊ አሰልጣኞችን ለማሰልጠን ታቅዶ 544ቱን ማሰልጠን የተቻለ ሲሆን እነዚህም በየክልላቸው የተለዩ የሂሳብና ሳይንስ መምህራንን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ስልጠናው በተግባር የተደገፈ መሆኑ ተማሪዎቹ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ማደግ መሰረት የሆኑትን የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶችን በይበልጥ እንዲረዱት በማድረግ ክህሎትና እውቀታቸውን አሳድገው የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ አቅም እንደሚፈጥርላቸው አቶ በላይነህ አስረድተዋል፡፡

በተለይም ለሂሳብና ሳይንስ የትምህርት አይነቶች ትኩረት በመስጠት እንዲህ አይነት ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን ማዘጋጀት ተማሪዎች በየደረጃው ሊያውቋቸው የሚገባቸውን እውቀቶች አግኝተው እንዲሄዱ ከማድረጉም ባሻገር መንግስት ያስቀመጠውን 7030 የመስኮች ምጣኔ ለማስጠበቅ የላቀ አስዋጽኦ እንደሚያበረክት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን የተሳካና ውጤታማ ለማድረግ የስልጠና ሞጁሎች ተዘጋጅተው እንደነበር አቶ በላይነህ ጠቅሰው በክልል፣ በክላስተርና በትምህርት ቤቶች ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የስልጠና መመሪያና በሳይንስና ሂሳብ የትምህርት አይነቶች መጻህፍት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው በሰባተኛና በስምንተኛ ክፍሎች በሙከራ ፕሮጀክት የተሰራ እንደነበር የሚናገሩት አቶ በላይነህ በቀጣይ በዘጠነኛና በአስረኛ ክፍሎች እንዲሁም በአምስተኛና በስድስተኛ ክፍሎች ለመስጠት የመማር ማስተማሩን ሂደት ክፍተቶች የመለየት ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ባለሙያዎችና የህዝብ ክንፎች ተሳታፊ ሲሆኑ በስልጠና አሰጣጥ ሂደቱ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አደረጃጀት ወጥ ያለመሆንና የበጀት እጥረት ገጥሟቸው እንደነበር ጠቁመው የቀጣይ የስድስት ወራት እቅድ ላይ በጋራ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ በመድረስ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማቸውን አጠናቀዋል፡፡

 

 


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡