የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከሐምሌ 4 እስከ ሐምሌ 7 2008 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከሐምሌ 4 እስከ ሐምሌ 7 2008 ዓ.ም ድረስ ይሰጣል

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከግንቦት 22 ጀምሮ ለአራት ቀናት ሊሰጥ የነበረው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በፈተና ወረቀቶች መውጣትና ቀድሞ በማህበራዊ ድህረ ገፅ መሰራጨቱን ተከቶሎ ፈተናው መቋረጡንና የድጋሚ ፈተና ቀን ከሰኔ 27-30/2008 . እንደሚሰጥ ለህዝብና ለተፈታኝ ተማሪዎች ማሳወቁ የሚታወቅ ነው፡፡

ይሁንና ይህ ጊዜ ከረመዳን ፆም ወር ጋር የተገናኘ መሆኑን በመግለፅ የኢትዮጵያ አስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለተማሪዎች ከፆም በኋላ እንዲሆን ያቀረበውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ከክልሎች ጋር በተደረገው ምክክር ጥያቄው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃሳብ መሆኑን ሚኒስቴር /ቤቱ ለመገንዘብ መቻሉን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ሌሎች ተማሪዎችና ወላጆቻቸውም የጓደኞቻቸውንና የወላጆቻቸውን ጥያቄ ይጋሩታል የሚል እምነት በመያዝ ፈተናው ከሐምሌ 4 ሰኞ እስከ ሐምሌ 7 ሐሙስ 2008 . ድረስ እንዲሰጥ መወሰኑን ትምህርት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት አስታውቋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሁሉም ዝግጅቶች በተሟላና በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተፈፀሙ መሆኑንና በእለቱ ሐምሌ 4 ቀን 2008 . ሁሉም ተማሪዎች የመለያ ካርዳቸውን /ID - Card/ በመያዝ በተመደቡበት ትምህርት ቤታቸው እንዲገኙ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አስተላልፋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውንና መምህራንን በማስተባበር ተማሪዎች በተረጋጋ መንገድ የትምህርት ክለሳ እንዲያደርጉ፣ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙና እንዲያደርጉ እንዲሁም ወላጆችም ቀጣዩን አንድ ወር ልጆቻቸውን እንዲደግፉ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጥሪውን አስተላልፏል፡፡


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡