የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የ2009 በጀት አመት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የምክክር መድረክ ተካሄደ

የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የ2009 በጀት አመት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የምክክር መድረክ ተካሄደ

የ2009 በጀት አመት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የምክክር መድረክ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት ከጥር 25-27/2009 ዓ.ም በደሴ ከተማ የተካሄደ ሲሆን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የተከበሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም በዕለቱ በቦታው በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ውስጥ የሚከተሉትን መልዕክት አስተላልፈዋል። በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማስፈን፣በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ከክልሉ መንግሥትና ህዝብ ጋር አብረው ለመሥራት  እንዲችሉ የእርስ በርስ መማማሪያና ተሞክሮ መለዋወጫ እድል እንዲኖራቸው ለማስቻል የጋራ ፎረም አቋቁመው በየሩብ አመቱ እየተገናኙ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ወቅት የሚታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥናትና ምርምር ሊደረግባቸው በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑንና በቅርቡም የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ይፈራረማሉ ተብለው እንደሚጠበቁ ገልጸዋል። የተከበሩ አቶ ብናልፍ አክለው የቅድመ መደበኛ ትምህርን የማሳደግ፣በተለይ በገጠር አከባቢ ከፍተኛ የሆነውን መጠነ ማቋረጥና የትምህርት ቀናትን የማሳነስ ችግሮች ለመቅረፍ፣የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን የማሰደግ ሥራ እና በልዩ ፍላጎት ትምህርት ዙሪያ የሚታዩ  ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲቀረፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

Newsየኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማሪያም በዕለቱ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የሚከተሉትን መልዕክቶች አስተላልፈዋል። ከዋናው መድረክ ቀደም ብለው በተካሄዱ 11ኛው የሴቶች ፎረምና በሦስቱም ዘርፎች በተናጠል በተካሄዱ መድረኮች ላይ የተለዩበት አግባብ  እንደ ነበረ፣ የተጣሉ ግቦችን ለመፈጸም ያደረግነው ጥረትና ያስመዘገብናቸው ውጤቶ በቀሪው የበጀት አመቱ ጊዜያት ለሚኖረን አፈጻጸም እንደ መነሻ የሚወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና አምስተኛውን የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ልማት መርሃ-ግብርን ለማሳካት ካስቀመጥናቸው ግቦች አንጻር ተጨማሪ ርብርብ የሚጠይቁ በርካታ ጉዳዮች ስላሉ  በጥልቀት ፈትሸን በቀጣይ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ መገዘብና መግባባት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል። እያደጉ በሚሄዱ የትምህርትና ሥልጠና እርከኖች ላይ አጠቃላይ የሴቶች ተሳትፎንና የሴት አመራሮች ተሳትፎን ከማሳደግ አንጻር ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት መደረግ እንዳለበት፣በተለይ በተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት የሴቶች ተሳትፎንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበት አስገንዘበዋል። ክቡር ሚኒስትሩ በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የቅድመ መደበኛና መደበኛ ትምህርት መጠነ ማቋረጥና መድገም እንዲቀንስ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እና የትምህርት ጥራት ማረጋገጨ ፓኬጆች በተሟላ መልኩ እንዲተገበሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ፣በተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትና በልዩ ፍለጎት ትምህርት ፕሮግራሞች የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ከባለድርሻ አካል ጋር በሚገባ ተቀናጅቶ መረባረብ አስፈለጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ እየተተገበረ ያለውን የውጤት ተኮር ሥልጠና ሥርዓት በማጠናከር ብቁና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ማፍራት፣የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች የተሟላ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የእንዱስትሪ ኤክስቴሽን ሥራዎችን በዚህ ዘርፍ የሚሠሩ ሥራዎች ከጫፍ ጫፍ የተናበቡና የተመጋገቡ እንዲሁም ጥራትና ውጤታማነትን መሠረት ያደረጉ መሆን እዳለባቸው ገልጸዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮኣቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል የአመራር ሥርዓቱን ማስተካከል፣ስታንዳርዶችን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ፣ የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችንና የነባር ዩኒቨርሲቲዎችን የማስፋፊያ ግንባታ አፈጻጸምን ማፈጠን፣የሀብት አጠቃቀም ሥርዓትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ድጋፎችን መስጠት፣የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን በሚገባ መረባረብ እና ለ2010 የተማሪዎች ቅበላ አስፈላጊውን ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ተጠቁመዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አክለው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዙሪያቸው የሚገኙ የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማትንና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማን በመደገፍ እና በተለይም በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያና የትምህርትና ሥልጠና ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በፍጥነት በማስፋት ዘርፈ ብዙ ርብርብ ልደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

Newsበመድረኩ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ የስድስት ወራት የቁልፍና አባይተ ሥራዎች አፈጻጸም ሪፖርት፣የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ያለበትን ደረጃ የሚገልጽ ሪፖርት፣ ሰላማዊ መማር ማስተማር ማረጋገጥን በተመለከተ የውይይት መነሻ ሀሳብ፣በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ውጤታማነት ላይ የተካሄዱ ጥናቶች፣የትምህርት ተቋማት አመራር፤በውጤታማነት አሠራር (Deliverology) የአፈጻጸም ስልት ላይ፤የአድግራት ዩኒቨርሲቲ ሁሉንም ሥራዎች በልማት ሠራዊት አግባብ ለመፈጸም በማድረግ ላይ ያለው ጥረትና ያገኛቸው ውጤቶች እና የመሳሰሉት ተያያዥ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸው ከስምምነት ተደርሶባቸዋል።

በመጨረሻም የቀጣይ የ2009 በጀት አመት የዘጠን ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የምክክር መድረክ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር እንደሚካሄድ ተወስኖ መድረኩ ፍጻሜውን አግኝቷል።


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡