በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሁዋዌ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ይቋቋማሉ

በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሁዋዌ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ይቋቋማሉ

በሁሉም የሀገሪቱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሁዋዌ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ጥር 1/2009 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴርና ሁዋዌ በተሰኘው ዓለም አቀፍ የቻይና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ መካከል ተፈረመ።ስምምነቱን በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌና የሁዋዌ ኩባንያ  ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አዳም ማ ፈርመዋል። ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው  በወቅቱ ለጋዜጠኖች በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ሥራች ስከናወኑ እንደቆዩና ከነዚህም ሥራዎች መካከልም የዩኒቨርሲቲ እንዱስትሪ ቁርኝት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።ይህ በስምምነቱ መሠረት የሚቋቋመው በምጻረ ቃሉ “ HAINA” የተሸኘው የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መቋቋሙ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን በማሻሻልና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ አካዳሚዎቹ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ቆይታቸው ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በተግባር የተደገፋ የተለያዩ የአይሲቲ ሙያዎች ባለቤት ሆነው በገበያው ላይ ተፈላጊነታቸው  እንድጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የሁዋዌ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አዳም ማ እንደተናገሩት፤ኩባንያው በኢትዮጵያ  በሞባይል ኔትዎርክና በሌሎቹም ተያያዥ የቴሌኮም መሠረተ-ልማቶች ዝርጋታ ሰፊ ሥራዎችን ሲሠራ የቆያ እንደመሆኑ መጠን  ይህ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መከፈቱ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማካሄድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰው ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ በኩባንያው አካዳሚ ውስጥ አልፈው ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ በዘርፉ የተሻለ ክህሎት ይዘው እንደሚወጡ እና ራሳቸውንና ሀገራቸውንም የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ።ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አክለው፤ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በቴሌኮም መሠረተ-ልማት ዝርጋታም ሆነ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች የዓለም ገበያ ድርሻውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ መምጣቱንም ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ትምህርትና ምርምር ኔትዎርክ ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘላለም አሰፋ በበኩላቸው  እንደተናገሩት፤ የእንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ቁርኝትን ማጠናከር አንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተልዕኮ እንደመሆኑ መጠን እንደዚህ አይነቱ በተግባር የተደገፈ በእንዱስትሪዎች አማካኝነት የሚሰጡ ኮርሶች ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው  በተጨማሪ ተጨባጭ የሥራ ዓለም ክህሎትን ይዘው እንዲወጡ  ከማድረጉም በላይ ለፈጠራ ሥራም በር የሚከፍት በመሆኑ ከኩባንያው ጋር ቁርኝት ፈጥሮ መሥራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን  ጠቅሰው በቁርኝቱ መሠረት ተማሪዎች በአካዳሚው የሚሰጠውን ተግባር ተኮር ትምህርት ተከታትለው ሲያጠናቅቁ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሰርተፊኬት እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል። አቶ ዘላለም አካዳሚው ሥራ የሚጀምርበትንና የቆይታ ጊዚውን በሚመለከት በጋዜጠኞች ተጠይቀው፤ ሥራውን ለማስጀመር በኩባንያው በኩል የቤተ- ሙከራ ዕቃዎች እንደሚሰጡ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችን በመሰብሰብ ስለአካዳሚው ገለጻ እንደሚሰጣቸው፣ በመቀጠል ከኩባንያው ጋር  በመሆን ሥራውን በባለቤትነት የሚያንቀሳቅሱ ለሙያው ቅርበት ያላቸው የዩኒቨርሲቲ አካላት ተጠርተው ጥልቀት ያለው የአሰልጣኞች ሥልጠና ከተሰጠ  በኋላ በዚህ አመት መጨረሻ አከባቢ አካዳሚው ሥራ እንደሚጀምር ጠቅሰው የአካዳሚውን የህልውና ጊዜ በሚመለከት ለተጠየቀው  ጥያቄ፤ ሀገራችን የኩባንያውን ምርት እስከ ተጠቀመችና የኩባንያው ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ አሁን ባለው ሁኔታና ከዚህም በላይ ሆኖ እስከ ቀጠለ ድረስ የአካዳሚው ህልውና በዩኒቨርሲቲዎቻችን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡