ከነገ ጀምሮ በሁሉም የትምህርት መዋቅሮች ስልጠናና ውይይት እንደሚካሄድ ተገለፀ

ከነገ ጀምሮ በሁሉም የትምህርት መዋቅሮች ስልጠናና ውይይት እንደሚካሄድ ተገለፀ

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንደተናገሩት የስልጠናው ዓላማ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ በማድረግ፣የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ፣ የትምህርት ተሳትፎን በማረጋገጥ በአጠቃላይ ትምህርት፣በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት እንዲሁም የተማሪዎች ሥነ ምግባር እና ውጤታማነት በማረጋገጥ በኩል ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን የበለጠ ለማጎልበት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡MOE

ባለፉት ዓመታት ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር ሲካሄዱ ከነበሩ ውይይቶች መልካም ልምዶች መገኘታቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ከወላጆች ጋር የሚደረግ ውይይት መኖሩ የዘንድሮውን ስልጠና ለየት ያደርገዋል ያሉት ሚኒስትሩ እና ከ8ኛ ክፍል በላይና በዩኒቨርሲቲዎች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች የስልጠናው ተካፋይ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ፣በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራን በሙሉ በስልጠናው እንደሚሳተፉ አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡ 

በመቀጠልም በአጠቃላይ ትምህርት ከስምንተኛ ክፍል በላይ ለሚማሩ ተማሪዎች የስልጠና መድረኮች እንደሚዘጋጁ የተናገሩት ሚኒስትሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ነባር ተማሪዎች እንዲሁም ለአዲስ ተማሪዎች በተከታታይ ስልጠናው እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ የስልጠና መድረኮች ተዘጋጅተው እንደነበረ ያወሱት አቶ ሽፈራው ለመንግስት ግብዓት የሚሆኑ እንዲሁም ለስራችን የሚጠቅሙ ሃሳቦች አግኝተናል ብለዋል፡፡

ሀገራችን ባለፉት 25 ዓመታት ከማሽቆልቆል ጉዞ ወጥታ የልማት፣የዴሞክራሲና የሰላም ግንባታ ባካሄደችባቸው ዓመታት ውስጥ ትምህርት የነበረውን ድርሻ ፣የፌዴራል ስርዓት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የጋራ ማህበረሰብ የመፍጠር አስፈላጊነት በሚሉ አጀንዳዎች ዙሪያ በዩኒቨርሲቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ውይይት የሚካሄድ ሲሆን በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የሚካሄደው ውይይት የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት ስኬቶችና በሂደት የታዩ ጉድለቶች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሁን ያለውን የትምህርት ተሳትፎ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ብሎም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው ያሉት ሚኒስትሩ ብቁ፣ተወዳዳሪና ሀገሩን የሚወድ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ባህል ያለው ዜጋ ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል፡፡moe


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡