ዓላማችን የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ማሻሻል ነው! - የተማሪዎች ፓርላማ

ዓላማችን የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ማሻሻል ነው! - የተማሪዎች ፓርላማ

የፓርላማው አባላት ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ‹‹ዓላማችን የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ማሻሻል ነው!›› የሚል በትልቁ የተፃፈ መፈክር በአዳራሹ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ይታያል፡፡ ዋና አፈጉባኤዋ ኢክራም መህዲ የእለቱን አጀንዳ በአጭሩ በማስተዋወቅ ነበር ስራቸውን የጀመሩት፡፡ ‹‹ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የትምህርት ሚኒስቴርን የስራ አፈፃጸም ሪፖርት በማዳመጥ ይወያያል በመሆኑም ዕድሉን ለትምህርት ሚኒስትሯ እሰጣለሁ፡፡››

‹‹አመሰግናለሁ ክብርት አፈ ጉባኤ›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የትምህርት ሚኒስትሯ የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች በዝርዝር አቀረቡ፡፡ በተለይም የወላጅ መምህር ኮሚቴ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት፣ተማሪዎች የተሻሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልፀው በተለይም የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሌሎች ክፍሎችም ሆኑ ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን በመግለጽ ሪፖርታቸውን አጠቃለሉ፡፡

<<በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄ ወይም አስተያየት ካለ?>>አፈጉባኤዋ ጠየቁ፤ ውይይቱ ቀጠለ…..

ይሄ የየትኛው ሀገር ፓርላማ ነው? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ አያጠራጥርም፡፡ ፓርላማው ያለው እዚሁ ሃገራችን ውስጥ ለዚያውም በአንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ የጀግኖች መታሰቢያ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት መገኛው ደግሞ ሐረር ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከወራሪው የሶማሊያ ጦር ጋር በተደረገ ጦርነት አባቶቻቸውን ላጡ ልጆች ብቻ ማስተማሪያ እንዲሆን በ1958 ዓ.ም የተመሰረተው የጀግኖች መታሰቢያ ት/ቤት ዛሬ የአካባቢውን ማህበረሰብ ልጆች በአንድነት እያስተማረ ይገኛል፡፡

ትምህርት ቤቱ የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል፣መጠነ መድገምና ማቋረጥን ለመቀነስ እንዲሁም ትምህርት ቤቱን ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ሲሆን በተለይ የተማሪዎች ፓርላማን እንዲቋቋም በማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት ግን ለት/ቤቱ አድናቆትን አትርፈውለታል፡፡  የተማሪዎች ፓርላማ የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል የሰራው ስራና እያስገኘ ያለው ውጤት ከትምህርት ቤቱ አልፎ ለሌሎች ትምህርት ቤቶችም በተሞክሮነት እየቀረበ ይገኛል፡፡

ፓርላማው በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ 50 አባላት አማካኝነት የሚመሠረት ነው፡፡እነዚህ የምክር ቤት አባላት ከአንድ ክፍል አንድ ተማሪ በሚል መርህ የሚወከሉ ሲሆን በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ አማካኝነት የአየር ሰዓት ተሰጥቷቸው ቅስቀሳ ያደርጋሉ፡፡ በተጨማሪም ቢመረጡ የሚሰሯቸውን ስራዎች / ትምህርት ቤታችንን ለተማሪዎች ምቹ እናደርጋለን፣ኩረጃን እናስቀራለን፣የተማሪ ስነምግባር እንዲሻሻል እንሰራለን….ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል/ እንዲሁም ፎቶግራፋቸውንና የመወዳደሪያ ምልክታቸውን የያዘ ፖስተር አዘጋጅተው በት/ቤቱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ይለጥፋሉ፡፡

ከነዚህ ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ውጤት ያገኙት እንደ ቅደም ተከተላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር፣አፈጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ ሆነው ይሰየማሉ፡፡በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ 10 ሚኒስትሮችን በአፈ ጉባኤዋ አማካኝነት አቅርበው ያሾማሉ፡፡የሚኒስትሮቹ ሹመት ፌዴራሉን መንግስት አወቃቀር መሰረት ያደረገ ሲሆን የፆታ ተዋፅኦን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡በዚህ መሰረት ከአፈጉባኤ በተጨማሪ የትምህርት ፣የፍትህና ጸጥታ፣የስነ ጾታ፣ባህልና ቱሪዝም ማስታወቂያ ሚኒስትርነት ቦታዎች በሴቶች የተያዙ የሃላፊነት ቦታዎች ናቸው፡፡

‹‹50 የሚባል ውጤት ዳግመኛ አንጠራም›› በሚል ትምህርት ቤቱ የያዘውን የውጤት ማሻሻል እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ከረዱት ምክንያቶች አንዱ የተጠናከረ የተማሪዎች ፓርላማ መኖሩ እንደሆነ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር ጨምሮ የተለያዩ መምህራን ሲናገሩ ሰምተናል፡፡  የተማሪዎችን አማካይ ውጤት በመጀመሪያው ሴሚስተር ከ 50 በመቶ ወደ 60 በመቶና ከዚያ በላይ እናደርሳለን የሚለውን ዕቅዳቸውን ያሳኩ መሆናቸውንና በሁለተኛው ሴሚስተር ደግሞ ከ75 በላይ ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የትምህርት ሚኒስትሯ አበባ ሀጎስ የተናገሩት፡፡በትምህርት ቤቱ የሚገኙ 1ሺ529 ተማሪዎች በ1ለ5 ተደራጅተው እና የጥናት ፕሮግራም አውጥተው ውጤትና ስነምግባርን ለማሻሻል እየሰሩ መሆናቸው ለታየው የውጤት መሻሻል ዋንኛው ምክንያት መሆኑን ነው የትምህርት ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጥያቄና መልስ ውድድሮች በየደረጃው የሚካሄዱ መሆናቸው ሌላው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እገዛ ያደረገ ተግባር ሆኗል፡፡ ፓርላማው የጥያቄና መልስ ውድድሩን የተማሪዎች የእውቀት ደረጃ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ይረዳዋል፡፡ በውድድሩ ተማሪዎች የሚያገኙት ውጤት ይተነተናል፡፡እናም ዝቅተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በመለየት የመደገፍ ስራ ይሰራል፡፡

ከሁሉም አስገራሚው ነገር የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑት አፈጉባኤዋ አስተማሪ በማይኖርባቸው የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች አስተማሪ ተክተው ተማሪዎችን ማስተማር መቻላቸው ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሯ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የተሰራው ስራና የተገኘው ውጤት ለሌላው ተሞክሮ ይሆናል ማለታቸውም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡  የፓርላማ አባላቱ በመደበኛ የግንኙነት ጊዜያቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችና ክርክሮች የሚያደርጉ መሆናቸው አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት ልምድ ያዳበሩ ተማሪዎች በመፍጠር ረገድ የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶችን የሚወክሉ በመሆናቸው የተለያዩ ማንነቶችንና ባህሎችን በማስተናገድ መቻቻልና ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የበኩላቸውን እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የጀግኖቹ ፓርላማ የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባርን ማሻሻል ዋንኛ ዓላማው አድርጎ ቢንቀሳቀስም ዴሞክራሲያዊ ባህላቸው የተገነባ ሀገር ወዳድ ዜጎች ለማፍራት ፣ተማሪዎች በእውቀትና በምክንያት ላይ የተመሰረተ ውሳኔዎችን የመወሰን ብቃት እንዲኖራቸው እንዲሁም  በትምህርት ቤቱ ሰላማዊና ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ሊበረታቱና ለሌሎችም ትምህርት ቤቶች በተሞክሮ መልክ ተቀምረው ሊቀርቡ ይገባል ፡፡


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡