የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም እቅድ አወጣጥ አፈጻጻም ድጋፍ ፣ክትትል፣ ግምገማና ማሻሻያ አተገባበር ላይ ስልጠና ተሰጣቸው

የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም እቅድ አወጣጥ አፈጻጻም ድጋፍ ፣ክትትል፣ ግምገማና ማሻሻያ አተገባበር ላይ ስልጠና ተሰጣቸው

የተማሪ ውጤት ለማሻሻል ትምህርት ቤቶች ለእቅድ ዝግጅት ግብዓት የሚሆን መረጃን መሰረት በማድረግ መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ::  የትምህርት ጥራትን ዕውን ለማድረግ ትምህርት ቤቶች መሰረት እንደመሆናቸው መጠን እቅዶቻቸውን ሲያዘጋጁ የተሟላ መረጃን መሰረት በማድረግ ማዘጋጀት እንደሚገባቸው በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ገለጸ።

ዳይሬክቶሬቱ የተማሪዎችን የመማር ሁኔታና የትምህርት ውጤት ለማሳደግ ከአራቱም ታዳጊ ክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ለተውጣጡ የትምህርት የትምህርት ቤት መሻሻል ባለሙያዎች/ ተጠሪዎች እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን ከትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም እቅድ አወጣጥ አስከ አፈጻጻም ድጋፍ ፣ክትትል፣ ግምገማና ማሻሻያ ማድረግ የሚያስችላቸውን እንዲሁም በትምህርት ቤት ድጎማ በጀት አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከየካቲት 16-20/2008 . በአዳማ ከተማ ጌጤ ሆቴል ሰጥቷል::

ስልጠናው መረጃን መሰረት ያደረገ የዕቅድ አዘገጃጀትና ውሳኔ አሰጣጥ በሚል ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማካሄድ ተከታታይነት ያለው የተማሪ ውጤት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የታቀዱና የተከናወኑ ጉልህ ተግባራት፣ በትምህርት ቤቶች እቅድ አፈጻጸም የተገኙ ውጤቶች ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በጥልቀት ተዳስሰዋል::

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት አማካሪ አቶ ያዕቆብ ሀብቴ እንደተናገሩት ስልጠናው የተዘጋጀበት አላማ ባለሙያዎቹ (የትምህርት መሻሻል ተጠሪዎች) ስለ ትምህርት ቤት መሻሻል ምንነት፣ ጠቀሜታው፣ ዓላማውና በትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ-ግብር የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም በዕቅድ ውስጥ የሚካተቱ ቁልፍ ተግባራትን ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር በተናበበና በተቀናጀ ሁኔታ ከመለየትም በዘለለ የግል ግምገማ በማካሄድ እንዲሁም መረጃን መሰረት በማድረግ ማቀድ፣ መተግበር፣ መደገፍና ማሻሻል እንዲቻል ግንዛቤ ለመስጠት ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አማካሪው አያይዘውም የትምህርት ቤት መሻሻል ዕቅድ ሲነደፍ የትምህርት ቤቶች ድጎማ በጀት በዋናነት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገባ መካከል የልዩ ፍላጎት ትምህርት ያላቸው ተማሪዎች የመለየትና ፍላጎታቸውን የሟሟላት ተግባር ለማከናወን የሚያስችል እንዲሁም የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎና ብቃት ሊያሳድግ የሚችል ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚገባ አማካሪው ተናግረዋል።

አቶ ያዕቆብ አክለውም የትምህርት ቤት መሻሻል መርሀ-ግብር ዋነኛ ትኩረት የተማሪዎች የመማር ማስተማር ተግባርና ውጤታማነት ላይ ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ትምህርት ቤቶች ደካማ እና ጠንካራ ጐናቸውን በመለየት ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መረጃን መስረት ያደረገ ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አማካሪው ጠቅሰው በመማር ማስተማር ተከታታይነት ያለው የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባር ማሻሻል፣ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደትን መፍጠር እንዲሁም ብቁና በቂ የትምህርት አመራርና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሀ-ግብር አማካሪ አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ ፈለቀ በበኩላቸው ሁሉንም የትምህርት ቤቶች የትኩረት አቅጣጫዎች በአንዴ ለመተግበር ስለሚያስቸግር የትምህርት ቤት መሻሻል ዕቅድ ዝግጅት መርሆችን በመከተል ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ በመገምገም የትምህርት ሂደቱን በማሻሻል ተማሪዎች የላቀ የትምህርት ውጤት እንዲያስመዘግቡ መረጃን በአግባቡ የመሰብሰብና የማደራጀት ስራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት ታዳጊ ክልሎች የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ አንዳንድ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም የተመዝጋቢ ቁጥር በመምህራን ጥረት እንዲጨምር የማድረግ፣ መጠነ ማቋረጥ የመቀነስ፣ ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩ ከወላጅ ተማሪ መምህር ህብረት ጋር በጋራ የመከታተልና የመደገፍ እንዲሁም በድጎማ በጀት አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተሰርተዋል።

እንዳንድ ተሳታፈዎች በበኩላቸው የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና የተማሪዎች ውጤት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በትምህርት ጥራትና ስኬት ዙሪያ በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።

በአዳማ ከተማ ጌጤ ሆቴል ከየካቲት 16-20/2008 . በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከትምህርት ቤት መሻሻል መርሃ ግብር ዳይሬክቶሬት፣ ከአራቱም ታዳጊ ክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የትምህርት ቤት መሻሻል ባለሙያዎች/ ተጠሪዎች እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡article5


ዜናዎች

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ኤድስ ተጋላጭነት፤

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤችአይቪ/ኤድስና ተያያዥ ጉዳዮች ዕቅድ አተገባበርና ውጤት በሚል ርዕሥ በአዳማ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሸማ ለማ በመድረኩ መክፈቻ ንግግራቸው እንደ ገለጹት በዚህን ሰዓት በሀገራችን 28 ሚሊዮን ማለትም ከ1/3ኛ በላይ ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙና ከእነዚህም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት አምራች ሃይል የሆኑት ወጣቶች ለኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ተጋላጭ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎች በሲስተር-ሲስተር፣ አቻ ለአቻ፣ የህይወት ክህሎት ፕሮግራሞች እንዲመካከሩ፣ የማስተባበሪያ አደረጃጀቶች እና ክበባትን ማቋቋም፣መርሀ-ግብር ማዘጋጀትና በዕቅድ አካተው የተሰራ ቢሆንም ተጋላጭነቱን ለመግታት የባህሪይ ለውጥ አሁንም አለመምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች በ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ላይ ተወያዩ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 በጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት ያከናወናቸውን ተግባራት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና መላው ሰራተኞች በተገኙበት ገምግሟል ፡፡ በግምገማው በርካታ ስኬታማ ስራዎች ቢሰሩም ከትምህርት ጥራት፣ ከትምህርት ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ከባለሙያዎች ክህሎት ማነስ ጋር የተያያዙ መጠነ ሰፊ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፎርም ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት፡

ተሳታፊ መምህራን ከ45ቱ የመንግስትና ከ4ቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቌማት የተውጣጡ 3ሺ175 ያህል ናቸው። በውይይቱም በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ለተነሱት ጥያቄዎች የመምህርነት ሙያ የተከበረ እንደሆነና በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ ለሚያጋጥሙና ለሚስተዋሉ ችግሮች መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቌማት አመራር በጋራ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሃ-ግብር 8,152 ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሐምሌ 7/2010 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎችም የስራ መመሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡