በትምህርት ዘርፍ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰነዶችን ሊተገበሩ ነው

በትምህርት ዘርፍ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰነዶችን ሊተገበሩ ነው

በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ጾታ ዳይሬክቶሬት በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሉ አምስት ሰነዶች ለሚኒስቴር /ቤቱ መካከለኛ አመራር አካላት እያስተዋወቀ ነው፡፡article (1)

በትውውቅ መድረኩ መግቢያ ላይ የስርዓተ ጾታ ዳይሬክተሯ / ኤልሳቤጥ ገሰሰ እንደገለፁት የተዘጋጁት ሰነዶች የስርዓተ ጾታ ማካተቻ ማንዋል፣ የሴቶች የትምህርት ስትራቴጂ፣ በትምህርት ቤቶች የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከል የወጣ መመሪያ፣ የስርዓተ ጾታ ምላሽ መስጫ ማሰልጠኛ ማንዋል እና ለሴቶች ድጋፍ መስጫ መመሪያ ናቸው። የመድረኩ ዋና ዓላማም መካከለኛ አመራሩ የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ካወጣቸው  ህጎች በተጨማሪ እነዚህን ሰነዶች በማስፈጸም ለስርዓተ ጾታ እኩልነት መስፈን የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ዳይክቶሬቱ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና በአራተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሀ ግብር በትምህርትና ስልጠና ዘርፉ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማስፈን ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እነዚህን ሰነዶች ለማሻሻልና ለማዘጋጀት አቅዶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

በዳይሬክቶሬቱ የክትትልና ድጋፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተመስገን ክበበው በበኩላቸው የሰነዶቹ ዝግጅትና ትውውቅ መደረግ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ አመራርና ድጋፍ ሰጪው ክፍል የስርዓተ ጾታ ጉዳዮችን በሶስት ዋና ዋና ፕሮግራሞች አካተው እንዲሰሩ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ 2015 የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር ለማጣጣም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን እየተዋወቁ ካሉት አምስት ሰነዶች በተጨማሪ ቀደም ሲል የህይወት ክህሎት ስልጠና ማንዋል፣ እያወቃችሁ እደጉ መጽሀፈ እድ እና ስትራቴጂያዊ አተገባበር ማእቀፍ የተሰኙ ሰነዶች ተዘጋጅተው አስከ ክልል ድረስ ላሉ /ቤቶች ተሰራጭተው አገልግሎት ላይ መዋላቸውንም አቶ ተመስገን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል / አሰፋሽ ተካልኝ እና አቶ እሸቱ ይመር የሀገራችንን እድገት ለማስቀጠል የሴቶች የልማት ተሳታፊነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የስርዓተ ጾታ ጉዳይን ከልማት እቅዶቻቸው ጋር በማካተት የተናበበና የተጠናከረ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡


ዜናዎች

የቀጣይ 5 ዓመት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር "የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለፍትሃዊነት " በሚል መሪ ቃል ለቀጣዩ 5 ዓመታት የሚተገበር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አካል ጉዳተኞች እንደየችሎታቸውና እንደየፍላጎታቸው መማር እንደሚገባችዉ ተገለጸ፤

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከሰኔ 04 - 11/2010 ዓ.ም በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ስታንዳርድ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱም ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ የአካቶ ትምህርትና የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፤ከትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ መሀመድ አህመዲን የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በፈተናው ሂደት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጅ፣ የሚዲያ አካላትና የፀጥታ ኃይል እንዲሁም መላው ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በአንዳንድ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው ክፍል መግባትና ለሌላ ተማሪ ለመፈተን የመሞከር አዝማሚያዎች ቢከሰቱም በየደረጃው በተሰማሩ የፈተናው ግብረ ኃይል አማካይነት ችግሮቹ እልባት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም ተጠናቀቀ

የ2010ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሠላም መጠናቀቁን በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርሁን ዱሬሳ ገለጹ፡፡ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች የተፈተኑት እና ከ70ሺህ በላይ የሚሆኑ ፈታኞችና ተቆጣጣሪዎች የተሳተፉበት ፈተና፣ በአንዳንድ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ሞባይል ይዘው ክፍል መግባት፣ ለመኮረጅ መሞከር፣ ለሌላ ተማሪ ለመፈተን መሞከር ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩ ቀላልና በፈተና ደንብ የሚታይ ይሆናል፣ በአጠቃላይ ግን ፈተናው በታቀደለት ጊዜ በሠላም ተጠናቋል ብለዋል ዶ/ር ዘርሁን፡፡

በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ተሠጠ፤

በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር በተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት አተገባበር ዙሪያ ከፌደራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና ከግንቦት 23-ግንቦት 27/2010 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው ፡፡